በምስራቅ ጎጃም ዞን በመኸር እርሻ ከ485 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን በመኸር እርሻ ከ485 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ይለማል
ደብረ ማርቆስ ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ጎጃም ዞን በመጭው የመኸር ምርት ዘመን ከ485 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እንቢአለ አለኽኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ከ669 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ ከ485 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በኩታ ገጠም እንደሚለማ ነው የተናገሩት።
በመኸር እርሻ የምርት ማሳደጊያ ግብአት ፣ ቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራሮችን በተሻለ መንገድ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ነው።
በዚህም አርሶ አደሩ ከራሱ አልፎ ለገበያ የሚያቀርበው ትርፍ ምርት ለማምረት እንደሚችልም ነው የተናገሩት።
ከ100 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የስንዴ፣ ጤፍ ፣ ማሽላ ፣ የቢራ ገብስ ፣ በቆሎና ቦለቄ ሰብሎችን በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገው ጥረትም ክረምቱ ቀድሞ በገባባቸው አካባቢዎች ከ90 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
በኩታ ገጠም ልማቱ ከ20 በላይ ትራክተሮች በእርሻ ስራው ላይ መሰማራታቸውን ጠቁመው ይሕም የአርሶ አደሩን ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት በመቆጠብ በሌሎች የልማት ስራዎች እንዲሰማራ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
እስካሁን በኩታ ገጠም በዘር ለተሸፈነው መሬትም ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ይህም ምርታማነትን በማሳደግ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዞኑ የደብረኤሊያስ ወረዳ የገነቴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አየነው በቀለ እንደገለጹት፤አንድ ሄክታር መሬታቸውን በኩታ ገጠም በማልማት በቆሎ መዝራታቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመትም በኩታ ገጠም ካለሙት ስንዴና በቆሎ ያገኙትን ተጨማሪ ምርት ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደጋቸውን አስረድተዋል።
የደጀን ወረዳ የኩራር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ያደለው በዛ በበኩላቸው፤ ባለፈው የምርት ዘመን ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በኩታ ገጠም ማሽላ በመዝራት ተጨማሪ የአራት ኩንታል ምርት እንዳገኙ ነው የሚገልጹት።
በዘንድሮ ዓመትም ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋት በአካባቢው ካሉ አርሶ አደሮች ጋር በጋራ በመሆን በኩታ ገጠም ማሽላን መዝራታቸውን አብራርተዋል።
የኩታ ገጠም አሰራር ዘርንና ግብአት አጠቃቀምን በተመሳሳይ ጊዜ ከማካሄድ ባሻገር የሚዛመት የሰብል በሽታን፣ አረምንና ተባይን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ በመኸር ምርት በአጠቃላይ ከሚለማው ከ669 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ26 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት መታቀዱንም ነው ያመለከቱት።