ቀጥታ፡

በክልሉ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎች ከአካባቢው ጸጋ እና ከኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር መጣጣም ይጠበቅባቸዋል

ወልቂጤ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጧቸው ስልጠናዎች ከአካባቢ ፀጋ እና ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር መጣጣም እንዳለባቸው የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በአዲሱ የቴክኒክና ሙያ የስልጠና መስክ ልየታ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና በወልቂጤ ከተማ ሰጥቷል፡፡


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ሰለሞን ፈርሻ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አዲሱ የስልጠና ልየታ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ገበያው እና ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ማፍራት ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስችል ነው።

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ተመስርተው የልህቀት ማዕከል በመሆን ዘመኑን የዋጀ እውቀትን ማስረጽ ላይ አተኩረው መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የአካባቢውን የልማት እንቅስቃሴ እና ጸጋ መጠቀም የሚችል የሰለጠነ ብቁ የሰው ሃይል በማፍራት የሰልጣኞችን ተመራጭነትና ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ አበራ ኤልያስ (ዶ/ር) ፤ ኮሌጆች በአካባቢያዊ ፀጋ እና በሥራ ገበያ ፍላጎት መሰረት  ወቅቱን የዋጀ ሙያ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ጥናት ተደርጓል ብለዋል።


 

ይህም ሰልጣኞች የተሻለ ክህሎትና እውቀት ይዘው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ተቋማቱ ተወዳዳሪ ዜጎችን በብዛት ለማፍራት ያስችላቸዋል ብለዋል።

የወራቤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አካዳሚክ ዘርፍ ምክትል ዲን ወይዘሮ ሶፍያ ዋበላ በበኩላቸው፤ አዲሱ የትምህርት ስልጠናና ስትራቴጂ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለትምህርትና ስልጠና ጥራት መረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።


 

ስትራቴጂው በኢንዱስትሪ እና በግብርና ዘርፍ ያሉ ፀጋዎችና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መንገድ በገበያው ተወዳዳሪ የሚሆኑ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

በአዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስኮች ልየታ አምራች፣ ግብርና፣ ቱሪዝም እና አገልግሎት ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ የስልጠና መስኮች የአካባቢ እና የሃገር እድገት ፍላጎትን መሰረት ያደረገ መሆኑ ለዘርፉ ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን የምስራቅ ጉራጌ ዞን ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መምሪያ ሃላፊ አቶ አህመዲን ጀማል ተናግረዋል። 


 

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የኢንዱስትሪውን ፍላጎት የሚያሟላ ብቃት ያለው የሰው ሀይል በተግባር እና በንድፈ-ሃሳብ ትምህርት ታግዘው እንዲያሰለጥኑ የሚያስችላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

በመድረኩ የክልሉ የዘርፉ አመራሮችን ጨምሮ የዞንና የልዩ ወረዳ የቴክኒክና ሙያ መምሪያ ሃላፊዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲኖች እና የዘርፉ አጥኚዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም