በክልሎች የመምህራንን አቅም በመገንባትና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁ ዜጋ የማፍራት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሎች የመምህራንን አቅም በመገንባትና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁ ዜጋ የማፍራት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል
ሆሳዕና/ዲላ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የመምህራንን አቅም በመገንባትና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽ በማድረግ ብቁ ዜጋ የማፍራት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሎቹ ትምህርት ቢሮዎች ገለጹ።
የሆሳዕና እና የዲላ ትምህርት ኮሌጆች በተለያዩ የትምህርት መሰኮች ያሰለጠኗቸውን 2ሺህ 20 እጩ መምህራንን በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዲፕሎማ እና በሰርተፍኬት ዛሬ አስመርቀዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፣ በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽ በማድረግ በእውቀት የበቁ ዜጎችን ለማፍራት እየተሰራ ነው።
የትምህርት ኮሌጁ ከቅድመ አንደኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ የሚያስተምሩ መምህራንን በብቃት በማሰልጠን ኮሌጁ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ክልሉ የበኩሉን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም በቀጣይ በስነ ምግባር የታነፁና ሀገራቸውን የሚያሳድጉ ዜጎችን ማፍራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በክልሉ የመምህራንን አቅም በመገንባትና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁ ዜጋ የማፍራት ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኮሌጁ ዲን አባይነህ ኤርጎጎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኮሌጁ በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ መሰረት ብቁ መምህራን እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬም ኮሌጁ ለ20ኛ ዙር በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዲፕሎማና በሰርተፍኬት ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 51 መምህራንን አስመርቋል ብለዋል።
በዲግሪ መርሀግብር ከእንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 98 በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ኤልሳቤት ፈለቀ፤ በኮሌጅ ቆይታዋ በቀጣይ ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት የሚያስችል እውቀት ማግኘቷን ተናግራለች።
መምህርነት ትውልድን በላቀ ትጋት፣ በታማኝነትና በቅንነት በመቅረፅ ረገድ ትልቅ ሀላፊነት ያለበት ሙያ መሆኑን ተናግራለች።
በኮሌጁ ባገኘው አውቀት በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቱን የተናገረው ደግሞ በዲፕሎማ መርሃ ግብር ከሒሳብ ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ደግነት ስምኦን ነው።
በተመሳሳይ የዲላ ትምህርት ኮሌጅ ለ13ኛ ዙር በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዲፕሎማና በሰርተፍኬት ያሰለጠናቸውን 969 እጩ መምህራንን ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃው ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ እንዳሉት፤ በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና የመምህራንን አቅም በማሳደግ የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።
የዲላ ትምህርት ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ ደረጃ መምህራን ማፍራቱ ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
መምህርነት ትውልድ የሚቀረጽበትና ሀገር የሚገነባበት ታላቅ ጥበብ ነው ያሉት ሃላፊው፣ እጩ ምሩቃን ያለባቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት ተገንዝበው ለትምህርት ጥራት መጠናከር የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ኮሌጁ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ መርሃ ግብር ማስመረቁ እለቱን ለየት ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የኮሌጅ ዲን ተረፈ ሾጣ ናቸው።
በዛሬው እለት በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዲፕሎማና በሰርተፍኬት ያሰለጠናቸውን 969 እጩ መምህራ መመረቃቸውን ገልጸዋል፣ ምሩቃን በቀጣይ ለሀገር እድገት የሚተጋ ትውልድ ለመፍጠር በሃላፊነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በኮሌጁ ከጄኔራል ሳይንስ ትምህርት ክፍል በመጀመሪያ ዲግሪ የዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው የምስራች ምትኩ በበኩሏ፤ መንግስት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የሰጠው ልዩ ትኩረት ዘርፉን ለመቀላቀል እንዳነሳሳት ገልጻለች።
በቀጣይ በመምህርነት ሙያዋ ሕጻናትን በጥሩ ስነምግባር ኮትኩቶ ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።