ቀጥታ፡

ጤናማና አምራች ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚከናወነው የተቀናጀ ጥረት ውጤት እየተገኘ ነው

ድሬዳዋ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ጤናማና አምራች ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚከናወነው የተቀናጀ ጥረት ውጤት እየተገኘ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አስታወቁ።

በድሬደዋ አስተዳደር  በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር  ወጪ የተገነባ የቢፍቱ አጠቃላይ ሆስፒታል ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።


 

ሆስፒታሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በተገኙበት ተመርቆ ስራ ጀምሯል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ እንደ አገር ጤናማ እና አምራች ህብረተሰብ ለመፍጠር የተከናወኑ የተቀናጁ  ስራዎች ውጤታማ ናቸው።

በተለይም ባለፉት አምስት  አመታት ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር  በመንግሥት እና በግል ባለሃብቶች የተከናውኑ ስራዎች አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስት ለረዠም አመት በስራ ላይ የቆየውን  የጤና ፖሊሲ በማሻሻል ወቅቱን የጠበቀና ዘመኑን የዋጃ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ስራ ላይ በዋለው የጤና ፖሊሲ በሽታን ከመከላከል ባሻገር አክሞ የማዳን ስራ ትኩረት ተሰጥቶት  መሠረታዊ ውጤት እንዲመዘገብ መደላድል መፍጠሩን አመልክተዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር በግል ባለሃብት ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ጠቅላላ ሆስፒታል የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ አመታት በአስተዳደሩ በከተማና በገጠር አካባቢዎች ጤናማና አምራች ማህበረሰብ ለመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።


 

አስተዳደሩ የጤና ፍትሃዊ ተደራሽነትና ጥራት እንዲረጋገጥ ባከናወናቸው ተግባራት ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው በዘርፉ ባለሀብቶች ሚናቸውን እንዲወጡም ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በዛሬው ዕለት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ጠቅላላ ሆስፒታል የዚሁ ውጤት መገለጫ መሆኑን ጠቁመዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው፤ የሆስፒታሉ ስራ መጀመር በጤናው አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል ።


 

ጠቅላላ ሆስፒታሉ  ዘመናዊ መሳሪያዎችና ክፍሎችን ያካተተና ዲጂታል የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  የሆስፒታሉ ባለቤት ዶክተር ሱሌይማን ኢብሳ ናቸው።


 

ሆስፒታሉ  ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቁመው ተገንብቶ ስራ እንዲጀምር በመንግስት በኩል ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም