በሸገር ከተማ የኢንቨስትመንት መስፋፋት የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድገትን እያፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ የኢንቨስትመንት መስፋፋት የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድገትን እያፋጠነ ነው
ሸገር ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦በሸገር ከተማ የኢንቨስትመንት መስፋፋት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የከተማዋን የኢኮኖሚ ዕድገት እያፋጠነው መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
አስተዳደሩ ይህንን የገለጸው ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈው 2ኛው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ኤክስፖ ፎረም በተካሄደበት ወቅት ነው።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በፎረሙ ላይ እንደተናገሩት፤ በዘርፉ የሚሰጡ የኢንቨስትመንት አገልግሎቶችና የአቀባበል ሥርዓቶችን ለማሻሻል ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጥ ማምጣት ተችሏል።
ባለፉት ዓመታት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ምቹና ሳቢ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የተሻለ ውጤት እየተገኘ መምጣቱንም ገልጸዋል።
የኢንቨስትመንት መስፋፋት የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድገትን እያፋጠነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከተማዋን የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው የተቀናጀ አሠራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የፎረሙ ዋና ዓላማ የኢንቨስትመንትን ውጤታማነት ማሳደግ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፤ በመንግሥትም ሆነ በባለሀብቶች በኩል የሚታዩ ጉድለቶችን በውይይት ለይቶ መፍትሔ ማስቀመጥ መቻሉን አስረድተዋል።
የሸገር ከተማ የኢንቨስትመንት ጽ/ቤት ኃላፊ ኃይለሚካኤል ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከተማዋ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሏት በርካታ ምቹ ዕድሎች እንዳሏት ገልጸዋል።
ለአብነትም የከተማዋን የመሬት አስተዳደር በቴክኖሎጂ በማገዝ አሠራሩን ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ባለፉት ሦስት ዓመታት 3 ሺህ 869 ብቻ የነበረው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቁጥር፣ በአሁኑ ወቅት በተከናወኑ አበረታች ሥራዎች ወደ 5 ሺህ 200 ማደጉን ኃላፊው ተናግረዋል።
ይህም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ለከተማዋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በፎረሙ ላይ የተሳተፉትና በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩት ባለሀብት አቶ ፍቃዱ ጉተማ እንደተናገሩት፤ መድረኩ መዘጋጀቱ ሥራቸውን ለማሳደግ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል።
በአሁኑ ወቅት በመንግሥት የተፈጠረው ምቹ የሥራ ሁኔታ አበረታች በመሆኑ፣ ሠርቶ ለመለወጥ ከፍተኛ መነቃቃት እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በፒፒሲ ፕላስቲክ ምርት ዘርፍ የተሰማሩት ወይዘሮ መጽሄት ከተማ በበኩላቸው፤ መንግሥት በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ወደ ሥራ በመግባታቸው ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውንና በከተማዋ ዕድገት ውስጥም የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።