በክልሉ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ውጤታማ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ውጤታማ ተግባራት ይጠናከራሉ
ኮምቦልቻ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም ሴቶች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሳድጉ፣ ሀብት እንዲያፈሩ፣ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና ከጥቃት እንዲጠበቁ ለመታደግ በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን በማሳደግ በውሳኔ ሰጪነትም አዎንታዊ ሚና እንዲኖራቸው መደረጉን ጠቅሰው፣ ውጤታማ ተግባራት በማከናወን ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።
በጤና ተቋማት የእናቶች ማቆያ እና የሴቶች ማገገሚያ ማዕከል እየተቋቋመ እንደሚገኝ የተናገሩት የቢሮ ኃላፊዋ፣ ለዚህም የተለያዩ ተቋማትና አጋር አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ደሳለኝ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዞኑ የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ሴቶች በመደገፍና የገንዘብ ብድር በመስጠት ወደሥራ ገብተው ገቢ እንዲያገኙና የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ሴቶችን በልማት ቡድን ጭምር በማደራጀት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ዘቢባ አህመድ ናቸው።
መንግስት፣ የተለያዩ ተቋማት እና አጋር አካላት ለሴቶች ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው የሚደርስባቸውን ጥቃት መከላከልና በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።