የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዛምቢያ አቻው ተሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዛምቢያ አቻው ተሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27 /2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛምቢያ ኢትዮጵያን 2 ለ 1 አሸንፋለች።
በንዶላ ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፍሪዳ ንዳሼ እና ፒዳ ሙዙዋ የዛምቢያን ጎሎች አስቆጥረዋል።
ምኅረት አየለ የኢትዮጵያን ብቸኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጪ ግብ ማስቆጠሯ በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን ለመቀልበስ ተስፋ የሚሰጥ ነው።
የሁለቱ ሀገራት የመልስ ጨዋታ ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ካሸነፈች በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፊፋ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ማለፏን ታረጋግጣለች።
10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ።
በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች። ቀሪ አራት ሀገራት በመጨረሻው ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ይለያሉ።