ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃና መስህብ መዳረሻ ልማት እመርታ የኢኮኖሚ አቅምን የሚያጎለብት ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃና መስህብ መዳረሻ ልማት እመርታ የኢኮኖሚ አቅምን የሚያጎለብት መሆኑን በኢትዮጵያ የፖርቹጋል፣ ካናዳና ሕንድ አምባሳደሮች ገለጹ።

በአዲስ አበባ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ የሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድን አባላት የዓለም ቅርስ የሆነው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝቱም ላይ 40 አምባሳደሮች እና ከ10 በላይ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የባህል ማዕከል ጉብኝት አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የፖርቹጋል አምባሳደር ሉዊስ ፔሬስትሬሎ ዶ ናሲሜንቶ በጉብኝቱ ወቅት፤ የቱሪዝም ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅምን ለመገንባት የቅርስ ጥበቃ ሥራ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም የቱሪዝም ኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳደግ የምታከናውነው የቅርስ ጥበቃና የአዳዲስ መዳረሻ ልማት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያና ፖርቹጋል መካከል ዘመናት ያስቆጠረውን የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ወደላቀ ምዕራፍ ለማሳደግም ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ኒኮላስ ሲማርድ በበኩላቸው፤ ላሊበላ ድንቅ የኪነ-ሕንፃ የጥበብ ውጤት መሆኑን በመጀመሪያ ጉብኝታቸው እንደተመለከቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ቅርሶችም ለቱሪስቶች መንፈስን የሚያድሱና ድንቅ ውበትን የተላበሱ የዓለም ሃብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ላሊበላ ድንቅ የጥበብ ውጤት ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ሥፍራውም የመንፈስ ሰላምና እርጋታን የሚቸር ድንቅ መንፈሳዊ ሥፍራ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ፤ በኢትዮጵያና ሕንድ መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት በተለያዩ መስኮች ዕድገት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና ሕንድ ታሪካዊ ወዳጅነትም በጥንታዊ ቅርሶችና ማራኪ የቱሪስት መስህብ መዳረሻ ስፍራዎች እንደሚያመሳስላቸው ገልጸዋል።

በጉብኝታቸውም ላሊበላ በዓለም ላይ ድንቅና ታሪካዊ ኪነ-ሕንፃ ጥበቦች መካከል ግንባር ቀደም የሆነ የጥንታዊ ስልጣኔ ትሩፋት መሆኑን ተናግረዋል።

የዲፕሎማቲክ ልዑካኑ ጉብኝትም የኢትዮጵያን ድንቅ ቅርሶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም