ላሊበላ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታላቅነት የሚያሳይ አስደናቂ ህያው ቅርስ ነው - የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ላሊበላ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታላቅነት የሚያሳይ አስደናቂ ህያው ቅርስ ነው - የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ ላሊበላ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታላቅነት የሚያሳይ የሰው ልጅ አስደናቂና ሕያው የሥራ ውጤት የሆነ ቅርስ መሆኑን ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድን አባላት ገለጹ።
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የዓለም ቅርስ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የባህል ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በዚህ የጉብኝት መርሃ ግብር ላይ 40 አምባሳደሮች እና ከ10 በላይ የሚሆኑ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድን አባላት ለኢዜአ እንደገለጹት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በመጎብኘታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ላይ የታደሙት የሜክሲኮ አምባሳደር አሌሃንድሮ ኤስቲቪል በበኩላቸው፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የኪነ-ህንጻ ጥበብ አድንቀዋል።
ከመሬት ከአንድ ዓለት ተፈልፍሎ የተሠራና ወደ ሰማይ የሚናገር የአስደናቂ የጥበብ ሚስጥር መገለጫ ነው ብለዋል።
እያንዳንዱ ማዕዘን፣ መስኮትና በር ከአንድ ነጠላ ድንጋይ የተቀረጸ በመሆኑ ለዓለም የሚታይ ታላቅ የአንድነት ምልክት መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር መሆኗን፥ እንደ ላሊበላ ያሉ ከምናብ በላይ የሆኑ አስደናቂ የጥበብ፣ የታሪክና የባህል ቅርስ ባለቤት መሆኗን ተመልክተናል ነው ያሉት።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የሮማኒያ አምባሳደር ዩሊያና ግሊጋ እንደገለጹት፤ የቅርስ ጥበቃ ስራ ታሪክን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
አምባሳደሯ አክለውም የአሁኑን እና የወደፊቱን ጊዜ ለመገንባት ያለፈውን ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ቅርሶችን ለመጠገን እና ለመንከባከብ እያደረገ ያለውን ጥረት በማድነቅ፥ ይህን ዓይነቱን ለትውልድ የሚሻገር ሥራ ሁሉም አጠናክሮ ሊያስቀጥለው ይገባል ነው ያሉት።
በአፍሪካ ህብረት የኩባ አምባሳደር ሉካስ ዶሚንጎ በበኩላቸው ላሊበላ የአፍሪካን ታላቅነት በግልጽ የሚያሳይ ህያው ቅርስ መሆኑን ጠቁመዋል።
አፍሪካ ለዓለም ሕዝብ ልታሳውቀው የሚገባ ባህል እና ወግ ያላት መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፣ አህጉሪቱን ሁልጊዜ ከችግር ጋር ብቻ አያይዞ የመግለጽ ሁኔታ መታረም እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
አፍሪካ በባህልና በወግ እጅግ ባለጸጋ መሆኗን ጠቅሰው፥ ይህንን እውነታ ለማስተዋወቅ ኢትዮጵያ የጀመረችው የቅርስ ጥበቃና የማስተዋወቅ ሥራ በአርዓያነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።