ቀጥታ፡

የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ልዑካን በታሪካዊቷ ላሊበላ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ልዑካን ቡድን አባላት በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።

ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ በዩኔስኮ በተመዘገበው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ነው የአረንጓዴ ዐሻራቸውን ያኖሩት።

በታሪካዊቷ የላሊበላ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኘው የዲፕሎማቲክ ልዑክ፣ ትናንት የዓለም ድንቅ ቅርስ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝታቸው በተጓዳኝም በዛሬው ዕለት በቅርስ መዳረሻው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሂደዋል።

የልዑካኑ የችግኝ ተከላ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከቅርስና አካባቢ ጥበቃ ጋር በአርዓያነት ተሰናስሎ የሚሰራበት መሆኑን ዓለም አቀፋዊ የልማት አጀንዳ መሆኑ ተገልጿል።

ጉብኝቱና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት፣ አስደናቂ የኪነ-ሕንጻ ጥበብና የባህል ዕሴቶችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ትልቅ አጋጣሚን ፈጥሯል።

ጉብኝቱም ኢትዮጵያ ለቱሪስቶች አስተማማኝና ማራኪ መዳረሻ መሆኗን ለዓለም በመገለጥ የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተገልጿል።

የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተወካዮች በቅርስ ስፍራው ችግኝ መትከላቸው፣ የዓለም ቅርሶችን የመንከባከብና የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ የመከላከል ዓለም አቀፋዊ ትብብር ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል።

የዲፕሎማቶች ጉብኝትና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ኢትዮጵያ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በመጠቀም ለመልካም ገጽታ ግንባታና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት አጋዥ ሚና ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም