ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስትራቴጂካዊ ፕሮግራሞችን በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ነው -ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27 /2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ስትራቴጂያዊ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን በውጤታማነት በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እያመጣች መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፅም አሰፋ (ዶ/ር) ገለፁ።

ለመጪው ትውልድ ጽዱ፣ ጤናማና አረንጓዴ ሀገር ለማስረከብ የተጀመረው የ"ጽዱ ኢትዮጵያን ለትውልድ" ሦስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ሦስተኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ባለፉት ሁለት ዙሮች የተገኙ ውጤቶችን በማስፋት ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ወሳኝ አቅም የሚፈጥር ነው።

ንቅናቄው ለዜጎች ጤናማና ንጹህ አካባቢ ለመፍጠር እና ለመጪው ትውልድ ፅዱ ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ ቁርጠኝነትን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

የከተሞች መስፋፋት፣ የፕላስቲክ ቆሻሻ መጨመር፣ የአደገኛ ኬሚካሎችና ቆሻሻዎች ተገቢ አያያዝ እጥረት፣ የድምፅ ብክለት እና ሌሎች የአካባቢ ችግሮች የዜጎችን ጤና፣ የአካባቢን ደህንነትና የዘላቂ ልማት ጉዞአችንን እየተፈታተኑ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በርካታ ስትራቴጂያዊ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።

የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ፣ የአየር ንብረትን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ የንፁህ ኃይል ሽግግር፣ የከተማ ኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች፣ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የሚከለክል ሕግ፣ እንዲሁም የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ የማስገባት ክልከላ የዚህ ቁርጠኝነት ተጨባጭ ማሳያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በመርሃ ግብሮቹ ትግበራም ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።

ሀገሪቱ ለአካባቢ ጥበቃና ለአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች እየወሰደቻቸው ያሉ የመፍትሔ እርምጃዎችና ያላት ቁርጠኝነት በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመከላከል እንደሀገር በየዓመቱ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት ነው ብለዋል።

በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን መሪነት እየተተገበረ የሚገኘው የፅዱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ንፁህና ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር እየተከናወኑ ካሉ ዓበይት ተግባራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ተቋማዊ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም የተለያዩ ህግጋት ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ(ዶ/ር)፥ ባለፉት ሁለት ዙሮች የተካሄዱ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄዎች ለአካባቢ ጥበቃ ውጤታማ ተግባራት የተከናወነባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር ከ15 ሚሊየን በላይ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ54 ሚሊየን በላይ ህዝብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች ተደራሽ በማድረግ በባለቤትነት እንዲሳተፉ መደረጉን አንስተዋል።

3ኛው ዙር ንቅናቄ የፕላስቲክ ብክለት፣ የአደገኛ ኬሚካሎችንና አደገኛ ቆሻሻዎችን መከላከል እንዲሁም የድምፅ ብክለትን መከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ለአካባቢ ጥበቃ መሰረት እየጣለ መሆኑን ገልጸው፥ ለስኬታማነቱ ጠንካራ የሕዝብ ተሳትፎና የጋራ ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም