ቀጥታ፡

የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የ2019 በጀት አመት ረቂቅ በጀት ከ12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ወሰነ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27 /2018 (ኢዜአ)፦ የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) የ2019 ዓ.ም የክልሉ መንግሥት ረቂቅ በጀት ከ12 ቢሊዮን 8 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ውሳኔ አስተላልፏል።

ካቢኔው በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የቀረበለትን የ2019 የበጀት አመት ረቂቅ በጀት ላይ በጥልቀት በመወያየትና ግብዓት በማከል ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል።

በዚህም መሰረት በክልል ደረጃ ከተያዘው በጀት 60 በመቶ ለካፒታል በጀት የተመደበ ሲሆን 38 በመቶው ደግሞ ለመደበኛ በጀት የሚውል ነው።

የበጀቱ ምንጭም በዋናነት በክልሉ ከተለያዩ ገቢዎች የሚሰበሰብ ገቢ እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማና ከሌሎች ምንጮች ታሳቢ መደረጉ ተገልጿል።

በጀቱ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ33 በመቶ ብልጫ አለው።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፤ በ2018 የበጀት አመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ስራ ትኩረት ይሰጣል።

በተለይም በገጠርና በከተማ የሕዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ሊመልሱ በሚችሉ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

ለገጠር እና ለከተማ ኮሪደር ልማት፣ ለንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ለትምህርትና ጤና ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

በጀቱ ቁጠባን መሰረት በማድረግ በተለይም የህዝቡን ህይወት በሚያሻሽሉና መሰረታዊ ጥያቄ በሚመልሱ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ነው ያሉት።

በድህነት ቅነሳ ዘርፎች ላይ ርብርብ እንደሚደረግም አመላክተዋል።

በወረዳ ደረጃ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ ለማስጀመር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ያመላከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ለህብረተሰቡ ፈጣን፣ ፍትሃዊና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

በክልሉ ገቢን አሟጦ ከመሰብሰብ አንፃር በትኩረት መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የክልሉ ኢኮኖሚ በሚያመነጨው ልክ በታቀደው ልክ መሰብሰብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱም በቀረበው የ2019 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ነው ወደ ክልሉ ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም