የአካባቢ ብክለትን መከላከል ከሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ጋር የተሳሰረ ብሔራዊ የልማትና ደኅንነት ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢ ብክለትን መከላከል ከሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ጋር የተሳሰረ ብሔራዊ የልማትና ደኅንነት ጉዳይ ነው
የአካባቢ ብክለትን መከላከል ከሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ጋር የተሳሰረ ብሔራዊ የልማትና ደኅንነት ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የአካባቢ ብክለትን መከላከልና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ከኢኮኖሚ ምርታማነትና ከሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ጋር የተሳሰሩ ብሔራዊ የልማትና ደኅንነት ጉዳዮች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት ለአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር መሆን መቻሏንም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 3ኛውን ዙር የ"ጽዱ ኢትዮጵያን ለትውልድ" ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በይፋ አስጀምረዋል።
በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በመላ ሀገሪቱ በመደመር መንግሥት እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ከተሞችን ጽዱ፣ አረንጓዴ፣ ውብ እንዲሁም ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረጉም ባሻገር፣ የቱሪስት መስሕብነታቸውን እያሳደገው መሆኑን ተናግረዋል።
ሦስተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄም ከእነዚህ ሀገራዊ መርሃ ግብሮች ጋር በተቀናጀ መልኩ እንደሚተገበር ገልጸዋል።
የፕላስቲክ ብክለት፣ የአደገኛ ቆሻሻዎች አያያዝ እና የድምፅ ብክለት ለአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆኑ ከሕዝብ ጤና፣ ከኢኮኖሚ ምርታማነት፣ ከኢንቨስትመንትና ከሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ጋር የተሳሰሩ ብሔራዊ የልማትና ደኅንነት ጉዳዮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
እነዚህን ተግዳሮቶች መፍታት የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገራችንን ዘላቂ ልማት፣ ተወዳዳሪነት እና የትውልዶችን የወደፊት ዕድል የሚወስን ሀገራዊ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነውም ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዙሮች የተካሄዱት የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የተሳተፉባቸውና ትልልቅ ስኬቶች የተመዘገቡባቸው መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሦስተኛው ዙር ንቅናቄም የቀደሙትን ጠንካራ ጎኖች በማጠናከር እንዲሁም የክትትል፣ የሪፖርት ሥርዓት እና የተቋማዊ ቅንጅት ክፍተቶችን በጥልቀት በመገምገም መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ንቅናቄው በግንዛቤ ፈጠራ ላይ ብቻ ሳይወሰን በሚለኩ ውጤቶች፣ በጠንካራ ክትትልና ግምገማ እንዲሁም በተቋማዊ ተጠያቂነት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በብክለት መከላከል፣ በአካባቢ ጥበቃና ተያያዥነት ባላቸው ሕጎች ዝርጋታና ተፈጻሚነት እንዲሁም በኅብረተሰብ ግንዛቤ ፈጠራ ላይ ተምሳሌታዊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የንቅናቄውን ስኬታማነት ለማረጋገጥ ሁሉም የክልል መንግሥታትና የከተማ አስተዳደሮች እንደየአካባቢያቸው ሁኔታ ግልጽ የትግበራ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ በጀት በመመደብና ጠንካራ የክትትልና ሪፖርት ሥርዓት በመዘርጋት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
በተለይም የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ ከንቲባዎችና የአካባቢ ጥበቃ ተቋማት አመራሮች የመሪነት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ለሀገራዊ ንቅናቄው መሳካት የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሴቶችና ወጣቶች በአንድነት እንዲንቀሳቀሱም ጠይቀዋል።
መጪው ትውልድ የሚረከባት ኢትዮጵያ ከሙስና፣ ከአድልዎና ከብልሹ አሠራር ብሎም ከአካባቢ ብክለት የጸዳች እንድትሆን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የተጀመረው ጉዞ ለጽዱ አካባቢ፣ ለጤናማ ማኅበረሰብ፣ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና ለተሻለች ኢትዮጵያ የሚደረግ የጋራ ጉዞ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለመጪው ትውልድ የምናስተላልፈው ትልቁ ቅርስ ጽዱ፣ አረንጓዴ፣ ጤናማ እና ዘላቂ ኢትዮጵያ መሆን አለበት ብለዋል።