ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በሁሉም የሙያ መስክ ብቁ ሠራዊት የመገንባት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በሁሉም መስክ ለስትራቴጂካዊ ተልዕኮዎች ብቁ የሆነ ሠራዊት የማፍራት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የ26ኛ ዙር እጩ ተመራቂ ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

ዘንድሮ የተመረቁት ተማሪዎች በኢንጅነሪንግ፣ በጤና ሣይንስ፣ በቢዝነስና በማህበራዊ ጥናት እንዲሁም በተለያዩ ስትራቴጂካዊ የትምህርት መስኮች እውቀት ያካበቱ መሆናቸው ተገልጿል።

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከፕሮፌሽናል ሰራዊት መገንቢያ ማእከላት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ስትራቴጂካዊ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ግንባር ቀደም ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ በማንሳት፥ የዘንድሮ ተመራቂዎችም የዚሁ ማሳያ ናቸው ብለዋል።

ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር በቀጣይ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርጋዴር ጀነራል ከበደ ረጋሳ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የሠራዊቱን አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከ77 በላይ መደበኛ የትምህርት ፕሮግራሞችን ቀርጾ ብቁ ሙያተኞችን እያፈራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው በማይቋረጥ የለውጥና የእድገት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀትና ሙያዊ ሥነ-ምግባር አጣምረው በተግባር ላይ እንዲያውሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከተመራቂዎች መካከል ተሻገር ደገፋ (ዶ/ር) በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በቂ እውቀት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ሕዝብንና ሠራዊቱን በተለያዩ የምርምር ሥራዎች ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የማዕረግ ተመራቂ ሕይወት ቸሩ የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ስኬታማ መሆኑን ጠቅሳ፣ በምትሰማራበት መስክ ያገኘችውን እውቀት በተገቢው መንገድ ለመተግበር ማቀዷን ተናግራለች።

በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ እውቀትና ዲሲፕሊንን መቅሰሟን የገለጸችው ደግሞ የማዕረግ ተመራቂዋ ኤልሻዳይ ነዋይ ናት።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሜካናይዝድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ከፍያለው አምዴ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ፣ የሠራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተመራቂ ቤተሰቦች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም