በዞኑ ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል
ሚዛን አማን፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በበጀት ዓመቱ ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የዞኑ ሥራና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ኮጁ በዳካች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአካባቢውን ጸጋ መሠረት በማድረግ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው።
በዚህም በ2018 በጀት ዓመት ከ20 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት።
የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በግብርና ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና አገልግሎት ዘርፍ እንዲሰማሩ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራን ለማጠናከርም የመስሪያና መሸጫ ቦታ፣ የመነሻ ብድር ፣ የገበያ ትስስር ፣ የህይወት ክህሎት ስልጠናን ጨምሮ በተቀናጀ መልኩ የተከናወኑት የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ውጤት አስገኝተዋል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ወደስራ ለገቡ ወጣቶች ከ163 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰራጨቱንም ነው የጠቀሱት።
የአካባቢውን ጸጋ በማልማት ወደ ሀብት ቀይሮ መጠቀም እንዲቻል በግብርና ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰው፤ ወጣቶቹ በተለይ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ላይ በስፋት መሰማራታቸው ስኬት እንዲመዘገብ አድርጓል ብለዋል።
ከሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች መካከል በሚዛን አማን ከተማ የ"ዕድገት ዶሮ እርባታ" ማኅበር ሰብሳቢ ወጣት ገበየሁ ሽፈራው ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታ በመጠቀም 1 ሺህ የሥጋና የእንቁላል ዶሮዎችን እያረቡ መሆኑን ተናግሯል።
በተሰማሩበት መስክ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ የዘርፉን ገበያ ለማረጋጋት እየተቻለ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
በቀጣይም ስራውን በማስፋት የበግና የወተት ላሞች እርባታ ላይ ለመሰማራት ማቀዳቸውን ነው ያመለከተው።
የ"ዕድገት ለሰላም" ማኅበር ሰብሳቢ ሚሚ በላቸው በበኩላቸው፤በተያዘው ዓመት በማህበር በመደራጀት በእንቁላል ምርት ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ባለው የመስሪያ ቦታ ድጋፍን ጨምሮ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ለውጤታማነታቸው ጉልህ ድርሻ እንዳለው ነው ያመለከቱት።