ቀጥታ፡

የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ህዝቦች አብሮነት መጎልበት አበክረው ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበርና ለህዝቦች አብሮነት መጎልበት አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ።

"ብቃት ያለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም" በሚል መሪ ሃሳብ የባለድርሻ አካላት ውይይትና ለሃቅ ማጣራት ሙያተኞች የሥልጠና መድረክ እየተካሄደ ነው።


 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ 73 የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ከባለስልጣኑ ፈቃድ ወስደው እየሰሩ ነው። 

አብዛኛው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ለሰላም፣ ዴሞክራሲ የሀገርን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ገንቢ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በባሕር በር ጉዳይና ገጽታ ግንባታ ላይ መገናኛ ብዙሃኑ የጀመሩት ውጤታማ ሥራም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አብዛኛው የበይነ መረብ የመገናኛ ብዙሃን ገንቢ ሚና እየተጫወቱ ቢሆንም የተወሰኑ ደግሞ ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ የሚሰሩ እንዳሉም ተናግረዋል።

የበይነ መገናኛ ብዙሃን የጋዜጠኝነት ሙያዊ መርህን በመከተል ሊሰሩ እንደሚገባም በተደረገ ክትትል መለየቱን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሀሰተኛ መረጃና ጥላቻ ንግግር ሥርጭት በመቆጠብ ለህዝቦች አንድነትና ትስስር መጠናከር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ሚና እንዲጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ  እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም