በዞኑ የግብርናውን ዘርፍ በሜካናይዜሽን በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እየታየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የግብርናውን ዘርፍ በሜካናይዜሽን በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እየታየ ነው
ሮቤ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን የግብርናውን ዘርፍ በሜካናይዜሽን በመደገፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እየታየ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ አመለከቱ።
አርሶ አደሩ የተሻሻሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ዝንባሌና ተግባር እየተሻሻለ መምጣት ለምርትና ምርታማነቱ ማደግ ተጠቃሽ መሆኑ ተመላክቷል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ፤መንግስት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሻሻል የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው።
ለአብነትም በበልግ እርሻ ከ256 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በተለያዩ የሰብል ዘሮች ማልማት መቻሉን አመልክተዋል።
አርሶ አደሩ የግብርና ሜካናይዜሽንና ሌሎች የተሻሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ 80 በመቶ የሚሆነውን መሬት ማልማት መቻላቸውን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የአርሶ አደሩ የሜካናይዜሽንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የጠቆሙት።
ይሕም በአንድ ሄክታር መሬት የስንዴ ማሳ በአማካይ ይመረት የነበረውን ከ20 ኩንታል የማይበልጥ ምርት ከ60 እስከ 70 ኩንታል ማምረት እንደተቻለም ነው የገለጹት።
ለምርትና ምርታማነት መጨመር ዋነኛው ምክንያት የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋት የተከናወኑ ተግባራት ትልቁን ፋይዳ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የዞኑ አርሶ አደሮች ትራክተርን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ማሽነሪዎችን በብድር እንኳ ማግኘት ያዳግታቸው እንደነበር ነው ያስታወቁት፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን አርሶ አደሩ የግብርና ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነጻ በብድር እንዲያገኝ መንግስት ከፍተኛ ስራ መስራቱን አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
በዞኑ በዝናብ ብቻ ሁለት ጊዜ የማምረት ፀጋ መኖሩን ጠቅሰው፤ ከበልግ በተጨማሪ በመኽሩ የምርት ወቅት ከ538 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች የማልማት አቅም መፈጠሩን አክለዋል።
ከዚህም ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የመሰብሰብ አቅም መፈጠሩን ገልፀዋል።
በዞኑ በዝናብ ውኃ ከሚለማው እርሻ ባሻገር የተለያዩ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም ከ170 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ አማራጭ ማልማት መቻሉን ጠቁመዋል።
ከ 6 ሚሊዮን ኩንታል ባላይ ምርት መሰብሰብ እንደተቻለም ነው ዋና አስተዳዳሪው የገለጹት።
የአርሶ አደሩን የግብርና ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ይበልጥ በማሻሻል ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ወደ አዲስ ምእራፍ ለማሸጋገር ለሚደረገው ሀገራዊ ግብ ስኬት ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም ነው የተናገሩት።