ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የአደጋ ቅድመ መከላከል ውጤታማነትን እያጎለበተ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተሞችን ውበት በማጎናጸፍ የአደጋ ቅድመ መከላከል ውጤታማነትን እያጎለበተ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።

የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አመራር፣ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል አካባቢ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል። 


 

በመርሃ ግብሩ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ያስቻለ ስኬታማ የልማት ንቅናቄ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ህዝቦቿን በማስተባበር በየዓመቱ በብሔራዊ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ የምትተክላቸው ችግኞች የአካባቢ ጥበቃን በማሳደግ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የጎርፍ፣ መሬት መንሸራተትና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ለአደጋ ቅድመ መከላከል ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

የአረንጓዴ ልማት ተምሳሌት ከተሞችን በማስፋፋትም ንጹህ አየርና ውብ ገጽታ የተላበሰ ምኅዳር እንዲፈጠር በማድረግም ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተሞችን ውበት በማጎናጸፍ የአደጋ ቅድመ መከላከል ውጤታማነትን እያጎለበተ ነውም ብለዋል፡፡


 

አዲስ አበባም የአረንጓዴ ውበት ምሳሌ ሆናለች ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ፤ በቀጣይም ማህበረሰቡ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተለመደውን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አሕመድ መሐመድ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአካባቢ ልማት ብቻ ሳይሆን የቅድመ አደጋ መከላከል ሥራ ነው ብለዋል።

በዚህም ባለድርሻ አካላት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የጎርፍና ተያያዥ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም