በጎንደር ከተማ የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን ከጎበኙ ቱሪስቶች 17 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን ከጎበኙ ቱሪስቶች 17 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል
ጎንደር፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ በጎንደር ከተማ የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን ከጎበኙ ቱሪስቶች 17 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የቅርስ ጥበቃና የቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አይቸው አዲሱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ ለቅርሶች እድሳት መደረጉና የኮሪደር ልማት መካሔዱ ጎብኝዎችን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በዋናነት የፋሲል አብያተ መንግስታት ላይ የተካሄደው ጥገናና እድሳት፣ በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የአረንጓዴና ሌሎች የልማት ስራዎች የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በከተማዋ የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን ከጎበኙ 43 ሺህ 365 የውጭና የሃገር ውስጥ ቱሪስቶች 17 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
ከጎብኝዎች ውስጥም ስድስት ሺህ 420 የሚሆኑት የውጭ አገራት ቱሪስቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የአገር ውስጥ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በቱሪዝም ልማቱ ከ120 በላይ ፎቶ አንሺዎችና አስጎብኚዎች በተጨማሪ 380 ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።
የቱሪስቶችን ደህንነትና ምቾት በመጠበቅ የቆይታ ጊዜያቸውን የበለጠ ለማራዘም ከትራንስፖርት፣ ሆቴሎችና አስጎብኝ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በቀጣይም ቅርሶች በመንከባከብ፣ በመጠበቅ ፣ በማልማትና በማስተዋወቅ በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋገጠዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስጎብኚዎች ማህበር ፀሐፊ ሙሉቀን ተገኘ በበኩላቸው ፤ከለውጡ ዓመታት በፊት በጎንደር ከተማ ቅርሶች በአስጊ ሁኔታ ላይ በመገኘታቸው ለጎብኝዎች ዝግ ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በከተማዋ የሚገኙ አብያተ መንግስታትና ሌሎች ቅርሶች ተጠግነውና ታድሰው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ መደረጉ የጎብኝዎች ቁጥር እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ነው ያነሱት።
በተለይ በጎብኝዎች ይነሱ የነበሩ የመጸዳጃ ቤት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመብራትና ሌሎች መሠረታዊ ችግሮች በመሟላታቸው የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እያስቻለ መሆኑን አብራርተዋል።
የተገኘው ለውጥም ለአስጎብኚዎችና በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንዳስቻለም አስረድተዋል።
ሌላኛው አስጎብኝ ሳለጌታ ነጋ በበኩሉ፤ የፋሲል አብያተ መንግስታትንና በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶች ታሪካዊ ይዘታቸውን ጠብቀው መታደሳቸው የጎብኚዎችን ቀልብ መሳብ አስችሏል ብለዋል።
የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ በማሳደግ በኢኮኖሚ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቱሪዝም ዘርፍ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።