የግንባታ ፕሮጀክቶችን በዲጂታል አሠራር ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ወደ ሙሉ ትግበራ ገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
የግንባታ ፕሮጀክቶችን በዲጂታል አሠራር ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ወደ ሙሉ ትግበራ ገብቷል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የግንባታ ፕሮጀክቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ማስገባቱን ገለጸ።
በዲጂታል 2030 ስትራቴጂ መሠረት የፕሮጀክቶችን አፈጻጸምና አስተዳደር በዲጂታል ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የመከታተል ግብን ለማሳካት ባለሥልጣኑ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ጋር በመተባበርም "ኮንስትራክሽን ሬጉላተሪ ኢንፎርሜሽን ሲስተም" የተሰኘ የዲጂታል ሥርዓት አልምቷል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ምዑዝ በድሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማዘመን ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
በተለይም ዘርፉን በቴክኖሎጂ የተደገፈና ቀልጣፋ ለማድረግ የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጂነር ምዑዝ፤ በአሁኑ ወቅት የዲጂታል አሠራርን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ባለሥልጣኑ ፕሮጀክቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ክትትል ማድረግ የሚያስችል "ኮንስትራክሽን ሬጉላተሪ ኢንፎርሜሽን ሲስተም" የተሰኘ ሥርዓት ከኢንሳ ጋር በመተባበር ማልማቱንም ጠቅሰዋል።
ይህ የዲጂታል ሥርዓት በሙከራ ደረጃ ተተግብሮ ውጤታማ መሆኑን በማንሳት፣ አሁን ላይ ወደ ሙሉ ትግበራ እየገባ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህም የግንባታዎችን ጥራትና ፍጥነት በአግባቡ በመከታተል የኮንስትራክሽን ዘርፉን ውጤታማነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል ብለዋል።
ይህ የቁጥጥር ሥርዓት የሕንጻ ግንባታዎችን ብቻ ሳይሆን፣ ከፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ የፕሮጀክትና የግብዓት ቁጥጥርን እንዲሁም አጠቃላይ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በዲጂታል መንገድ ለመከታተል የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
የአሠራር ሥርዓቱ ማንኛውም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት በተቀመጠለት ጊዜ፣ በጀትና ጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
ሥርዓቱ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ቢሮ ሆነው የትኞቹ ፕሮጀክቶች የት ቦታ ላይ እንደሚገኙና በምን ዓይነት የግንባታ ደረጃ ላይ እንዳሉ በቀላሉ ለመከታተል ያስችላቸዋል ብለዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ጥቅም ላይ የማዋል ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ጨምሮ፣ ብልሹ አሠራሮችን በማስቀረት ረገድ የቴክኖሎጂው ወደ ሥራ መግባት ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አመልክተዋል።
ግልጽነትን በመፍጠር ረገድም አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዘርፉን ከቢሮክራሲ ማነቆዎች በማላቀቅ የኢንቨስትመንት ከባቢውን እንደሚያሳልጥም አብራርተዋል።
በፈቃድ አሰጣጥ ሂደት ላይ የዲጂታላይዜሽን ሥራ በስፋትና በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም ወደ ተሟላ የዲጂታል ትግበራ ምዕራፍ እንድንሻገር ጠንካራ መሠረት ጥሏል ነው ያሉት።
ሥርዓቱ በዲጂታል 2030 ስትራቴጂ መሠረት የኢትዮጵያን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ ቀልጣፋና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ እንደሚያፋጥንም ጠቅሰዋል።
የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የሚሰጣቸውን ሥልጠናዎች ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት ስድስት የሚሆኑ የሥልጠና መስኮችን በቨርቹዋል (በበይነ-መረብ) መስጠት መጀመሩን ጠቁመዋል።
በኮንስትራክሽን ዲዛይን ዘርፍ ያለውን ክፍተት መቅረፍ የሚያስችል የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዘርጋቱንም ኢንጂነር ታምራት ገልጸዋል።
ይህ የዲዛይን ቴክኖሎጂ ወይም Building Information Modeling (BIM) የተሰኘው ሥርዓት፤ ሕንጻው በአካል ከመገንባቱ በፊት በዲጂታል መድረክ ላይ ቀድሞ ታይቶ እንዲሠራ የሚያደርግ መሆኑንና ይህም የግንባታ ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ ለማስጠበቅ እንደሚያስችል አብራርተዋል።