ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከዛምቢያ ጋር ይጫወታል


አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27 /2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ከዛምቢያ ጋር ታደርጋለች።

ጨዋታው ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በንዶላ ሌቪ  ምዋናዋሳ ስታዲየም ይካሄዳል።

በአሰልጣኝ ራውዳ አሊ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ዙር ደቡብ ሱዳንን በድምር ውጤት 8 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

በሁለተኛው ዙር ኢትዮጵያ ብሩንዲን በአጠቃላይ ውጤት 4 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

በካሮል ካኒዬምባ የሚሰለጥነው የዛምቢያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ዙር ሩዋንዳን በደርሶ መልስ ውጤት 4 ለ 1 አሸንፋለች።

ዛምቢያ በሁለተኛው ዙር ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን በድምር ውጤት 7 ለ 0 በመርታት ለወሳኙ ጨዋታ ደርሷል።

አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ ከዛምቢያ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ  ሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጓ ይታወቃል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ለጨዋታው  በሳምንቱ አጋማሽ ወደ ዛምቢያ አቅንቷል።

ለዛሬው ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በንዶላ ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም አከናውኗል።

ተጫዋቾቹ በሙሉ ጤንነት እና በጥሩ ሞራል ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ካሮል ካኒዬምባ ዛምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ላለባት ጨዋታ ለ35 ተጫዋቾች የመጀመሪያ ጥሪ ያደረገች ሲሆን  በመጨረሻ ስብስቡ የተቀነሰ ተጫዋች የለም።

የሁለቱ ሀገራት የመልስ ጨዋታ ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ካሸነፈች በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፊፋ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ማለፏን ታረጋግጣለች።

10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ።

በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች። ቀሪ አራት ሀገራት በመጨረሻው ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ይለያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም