ቀጥታ፡

ሞሮኮ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ካናዳ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።

ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ ካናዳ ከሞሮኮ በሂውስተን ስታዲየም ይጫወታሉ።

ካናዳ በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ደቡብ አፍሪካን 1 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።

የሰሜን አሜሪካዋ ሀገር በዓለም ዋንጫው 16 ውስጥ ስትገባ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሞሮኮ ኔዘርላንድስን በመርታት ሌላኛው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ተሸጋግራለች።

በጨዋታው ሞሮኮ በ120 ደቂቃ አንድ አቻ የተለያየች ሲሆን በመለያ ምት ተጋጣሚዋን 3 ለ 2 ረትታለች።

የአትላንስ አንበሶቹ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪካቸው 16 ውስጥ ሲገቡ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል።

ኳታር ከአራት ዓመት በፊት ባዘጋጀችው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ መርሐ ግብር ተገናኝተው ሞሮኮ 2 ለ 1 ማሸነፏ አይዘነጋም።

ሞሮኮ በወቅቱ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ድረስ ድንቅ ግስጋሴ በማድረግ በዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጨረሻ አራት ውስጥ የገባች የመጀመሪያ አፍሪካዊ ሀገር ሆናለች።

ብሔራዊ ቡድኖቹ እስከ አሁን ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሞሮኮ ሶስቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

ሞሮኮ የማሸነፉን የቅድሚያ ግምት ወስዳለች።

የሁለቱ ሀገራት አሸናፊ ከፓራጓይ እና ፈረንሳይ አሸናፊ ጋር በሩብ ፍጻሜው ይገናኛል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ፓራጓይ ከፈረንሳይ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ በፊላደልፊያ ስታዲየም ይጫወታሉ።




ፓራጓይ በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ሳትጠበቅ የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋን ጀርመንን በማሸነፍ 16 ወስጥ ገብታለች።

የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር በ120 ደቂቃ አንድ አቻ የወጣች ሲሆን በመለያ ምት 4 ለ 3 በማሸነፍ በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ማንም ያልገመተውን ውጤት አስመዝግባለች። ፓራጓይ 16 ውስጥ ስትገባ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ፈረንሳይ ስዊድንን በበማሸነፍ 16ቱን ተቀላቅላለች።

የዘንድሮውን ዓለም ዋንጫ የማንሳት ሰፊ ግምት ያገኘችው ፈረንሳይ ለሰባተኛ ጊዜ ወደ 16ት ውስጥ ገብታለች።

ፈረንሳይ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ 16 ውስጥ ተሸንፋ አታውቅም።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫው ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ፈረንሳይ ጨዋታዎቹን በድል ተወጥታለች።

ፈረንሳይ እ.አ.አ በ1998 ባዘጋጀችው 16ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 16 ውሰጥ ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር 1 ለ 0 ያሸነፈች ሲሆን እስከ መጨረሻው በመሄድ የመጀመሪያ ዋንጫዋን አንስታለች።

ስዊድን እ.አ.አ በ1958 ባዘጋጀችው ስድስተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ሁለት ተገናኝተው ፈረንሳይ 7 ለ 3 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነበት አሸንፋለች።

በዛሬው የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ፈረንሳይ የማሸነፉን ሰፊ የቅድሚያ ግምት ወስዳለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም