አምስት ጎሎች በተቆጠሩበት አስገራሚ ጨዋታ አርጀንቲና ኬፕቨርዴን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈች - ኢዜአ አማርኛ
አምስት ጎሎች በተቆጠሩበት አስገራሚ ጨዋታ አርጀንቲና ኬፕቨርዴን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር አርጀንቲና ኬፕቨርዴን 3 ለ 2 አሸንፋለች።
ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሚያሚ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ በ29ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል አርጀንቲናን መሪ አድርጓል።
ሌሮይ ዱአርቴ በ59ኛው ደቂቃ የኬፕቨርዴን የአቻነት ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ 30 ደቂቃ ተጨምሯል።
ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በ92ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል አርጀንቲናን በድጋሚ መሪ አድርጓል።
ሲዲኒ ሎፔዝ ካብራል በ103ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ላይ ባሳረፈው ጎል ኬፕቨርዴ አቻ ሆናለች።
የኬፕቨርዴው ተከላካይ ዲኔ ቦርጄስ በ111ኛው ደቂቃ ሜሲ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ በራሱ ላይ አስቆጥሮ አርጀንቲና አሸናፊ ሆናለች።
የ39 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ ሰባት በማድረስ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን መሪነቱን አጠናክሯል።
በአጠቃላይ በውድድሩ 20 ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቱን አስቀጥሏል።
በዓለም ዋንጫ በስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረ እና በውድድሩ ላይ 30ኛ ጨዋታውን ያደረገ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል።
ለአርጀንቲና 123ኛ ጎሉን ያስቆጠረ ሲሆን በአጠቃላይ 918ኛ ፕሮፌሽናል ግቡን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ አርጀንቲና 16 ውስጥ ገብታለች።
አርጀንቲና በቀጣዩ ዙር ከግብጽ ጋር ትጫወታለች።
የደሴቲቷ ሀገር ኬፕቨርዴ ያልተጠበቀ የዓለም ዋንጫ ጉዞዋ 32ቱ ላይ ተገቷል።
ከ500 ሺህ በላይ ህዝብ ያላት ኬፕቨርዴ በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዋ ያሳያቸው ብቃት አድናቆት አስችሯታል። የዘንድሮው ውድድር ክስተት ሆናለች።
በሶስት ጨዋታዎች አቻ በመውጣት ጥሎ ማለፍ የገባችው ኬፕቨርዴ የመጀመሪያ ሽንፈቷን አስተናግዳለች።
ኬፕቨርዴ በጨዋታው የዓለም ሻምፒዮናዋን አርጀንቲናን ፈትናለች።
የ40 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ቮዚኒሃ ያለቀላቸውን ኳሶችን በማዳን ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።