የኢትዮጵያን ቅርሶች የመጠበቅና ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የማዋል ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ቅርሶች የመጠበቅና ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የማዋል ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ቅርሶች የመጠበቅና ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የማዋል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ገለጹ።
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድን አባላት የዓለም ቅርስ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጎብኝተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግስት በቅርቡ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የመገንባት፣ ነባሮችን የማደስ እንዲሁም ፓርኮችን የመገንባትና የማስተዋወቅ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል።
ዛሬ 40 አምባሳደሮች እና ከ10 በላይ የሚሆኑ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት እና የባህል ማዕከልን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።
ይህ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ያደረገው ጉብኝት ለሀገሪቷ ቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ጠቀሜታዎችን ይዞ የሚመጣ መሆኑን አቶ ስለሺ አብራርተዋል።
አምባሳደሮቹ አካባቢውን ይበልጥ ለዓለም በማስተዋወቅ ቱሪስቶችን እንዲስቡ እና የአካባቢውን ምቹነት ተመልክተው የሀገራቸውን ባለሀብቶችና ዜጎች ወደዚህ እንዲጋብዙ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አንስተዋል።
በቅርስ ጥበቃና ዕድሳት ሥራዎች ላይ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ በር ይከፍታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የዕድሳትና የጥገና ሥራም በህብረተሰቡ ተሳትፎና ዘላቂነት ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ከዚህም በላይ የማይዳሰሱ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶችን ይበልጥ ለመጠበቅ የሚያስችል ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ መከናወኑን ጠቁመዋል።
መንግስት በቀጣይም የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ቅርሶች የመጠበቅ፣ ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የማዋል እና ለተተኪው ትውልድ የማስተላለፍ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።