ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ተደራሽነት እመርታ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ተደራሽነት እመርታ የሴቶችን የሥራ ጫና በማቃለል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑን የልማት አጋሮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኃይል አቅርቦትን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኔዘርላንድስ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጁሊ ግርሃም፤ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ለአካባቢ ተስማሚ አነስተኛ የኃይል ማከፋፈያዎች እየበለፀጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ድርጅቱ የሚያደርገው የልማት ተሳትፎም የህብረተሰቡን የቤት ውስጥ አገልግሎትና የመስኖ ሥርዓት የውሃ አቅርቦት መሰረተ ልማት በማሻሻል ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማሻሻል በግብርናው ዘርፍ ጭምር የሴቶችን የገቢ አቅም የሚያጎለብት ዕድል እየፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል።

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ የምርት ማቀዝቀዣና ማቆያዎችም ብክነትን በመቀነስ የሴቶችን የሥራ ጫና በእጅጉ እያቃለለ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም የንግድና ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ተቋማትን ትብብር በማሳደግ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን የኢነርጂና የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት በመደገፍ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የዓለም ባንክ የኢነርጂ ዘርፍ ባለሙያ ወንድአየሁ ደምሴ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የኃይል ማስፋፊያና ማከፋፈያ መስመር ዝርጋት መሰረተ ልማት የሚደግፍ የኢንቨስትመንት ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ተደራሽነት እመርታም የሴቶችን የሥራ ጫና በማቃለል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑን አንስተዋል።

የዓለም ባንክ በፕሮጀክት ፋይናንስ፣ የቴክኒክ፣ የጥናትና ምርምር እገዛም የበርካታ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

የሴቶችንና የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረትም የኃይልና የውሃ አቅርቦት መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም