ቀጥታ፡

ከብክለት ወደ ውበት፡ የቀበና ወንዝ አዲስ ገጽታ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእንጦጦ - ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም የቀበና ግድብ ፕሮጀክትን ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸው ይታወሳል።

አንድን ከተማ ህያውና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሚያደርጓት ዋና ዋና መገለጫዎች የተፈጥሮ አካባቢዎቿ፣ ወንዞቿና አረንጓዴ ስፍራዎቿ ናቸው። 

ይሁን እንጂ ለረጅም ዘመናት የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸው የውበት ምንጭ መሆናቸው ቀርቶ የቆሻሻ መጣያና የብክለት ማዕከል ሆነው መቆየታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። 

ዛሬ ላይ ግን ይህ ታሪክ እየተቀየረ፣ የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የሚቀይሩ አስደናቂ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀትና ውበት የፈጠረው የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት አንዱና ዋናው ማሳያ ነው።

ይህ በአሁኑ ወቅት የአይን ማረፊያ የሆነው ስፍራ ቀደም ሲል የነበረው ገጽታ እጅግ አስከፊ ነበር። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፤ ቀደም ሲል ከአካባቢው ማህበረሰብና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሚለቀቁ ቆሻሻዎች ሳቢያ በወንዙ ውስጥ ይፈስ የነበረው ውሃ በከፍተኛ ሁኔታ የተበከለ ነበር። 

ስፍራው በአይን ለማየት እንኳን እስከማይመች ድረስ የተበላሸና ለአካባቢው ነዋሪዎችም ትልቅ የጤናና የደህንነት ስጋት ደቅኖ የኖረ መሆኑን ያስታውሳሉ።

ሆኖም ግን፣ ለአካባቢው አዲስ ገጽታን ያላበሰው ይህ የልማት ስራ ማህበረሰቡን በእጅጉ አስደስቷል። ወደ መልካም ገጽታ የተለወጠው ይኸው የተፈጥሮ አካባቢ፣ ነዋሪዎች ምቹና ጤናማ መኖሪያ እንዲያገኙ የተደረገውን ጥረት ስኬታማነት በግልጽ ያሳያል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት የአከባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ገዛኸኝ ደሩ እንዳሉት የቀበና ወንዝ እና አካባቢው ቀደም ሲል ለኑሮ የማይመች፣ በቆሻሻና በመጥፎ ጠረን የሚታወቅ ነበር። 

በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የጤና እና የደህንነት ስጋት ደቅኖ የነበረውና ቆሻሻ መጣያ የነበረው ገደላማ ስፍራ፣ በአሁኑ ወቅት በአመርቂ ሁኔታ ጽድቶና ለምቶ ማየት ችለናል ብለዋል። 

ይህንን ማህበራዊና አካባቢያዊ ችግር ለመቅረፍ በተከናወኑ የልማትና የጽዳት ስራዎች፣ ስፍራው በአሁኑ ወቅት ውብና ለዓይን የሚማርክ እይታን መጎናጸፍ መቻሉን ጠቅሰዋል። 

ወይዘሮ እታፈራው መንግስቱ በበኩላቸው የቀበና ወንዝ ለረጅም ዘመናት ተበክሎ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን የተከናወነው የልማት ስራ ግን ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። 

በተለይም በወንዙ ላይ ግድብ መሰራቱ ይበልጥ ውብ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ፣ በአሁኑ ወቅት በእግር ለመጓዝ ምቹ መሆኑንም ጠቅሰው ቀደም ሲል የነበረው አስከፊ ገጽታ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ በማየቴ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡

የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት የወንዞችን ብክለት ከመቀነስ ባለፈ፣ የከተማን ገጽታ እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ላቀ የውበት ደረጃ ማሸጋገር እንደሚቻል የታየበት ትልቅ ስኬት ነው። 

ቀደም ሲል ከአካባቢው ማህበረሰብና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሚለቀቁ ቆሻሻዎችና በሚወጣው መጥፎ ጠረን ሳቢያ ወንዙ በከፍተኛ ሁኔታ የተበከለ ነበር ብለዋል።  

አቶ በየነ ድልነሳው እና አቶ ደረጄ በሰጡት አስተያየትም፤ ስፍራው በአይን ለማየት እንኳን እስከማይመች ድረስ የተበላሸ፣ ማህበረሰቡን ለተለያዩ የጤና እክሎችና ለደህንነት ስጋት ይዳርግ የነበረ የጤና ጠንቅ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይሁን እንጂ ይህንን ማህበራዊና አካባቢያዊ ችግር ለመቅረፍ በተከናወኑ የልማትና የጽዳት ስራዎች፣ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ላይ አመርቂ ለውጥ መምጣቱን ነዋሪዎቹ ይመሰክራሉ።

አሁን ላይ አካባቢው ትልቅ ለውጥ በማሳየት፣ ለነዋሪዎች ማራኪ የመኖሪያ ስፍራ ከመሆኑም በላይ ለህጻናትና ለአዋቂዎች ጭምር ታላቅ አማራጭ ምቹ የመዝናኛ ስፍራ መሆኑን የጠቆመው ደግሞ ወጣት አሸናፊ ነው፡፡ 

ይህ ፕሮጀክት የአካባቢውን ማህበራዊና የጤና ስጋቶች ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ፣ በተገቢው እቅድና ቁርጠኝነት ከተሰራ የተበከሉ የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን መልሶ ማልማትና ለከተማ ውበት ማዋል እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ሆኗል።

ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውሲሆን የተገኘውን ውበት ዘላቂ ለማድረግ ትልቅ አደራና የቤት ስራ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ 

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆንና ለረጅም ዓመታት አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሁላችንም በባለቤትነት ስሜት ልንጠብቀውና ልንንከባከበው ይገባል ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የለማውን ውበት ይዞ ለመቀጠል ማህበረሰቡ አካባቢውን በመንከባከብ ረገድ የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

87 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት የሚሸፍነውን እና 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ፕሮጀክቱ ከተማዋን ጽዱ ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሆኗል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም