ቀጥታ፡

ዘላቂ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጠው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ

በዮሐንስ ደርበው

ዐቅምን በመሰብሰብ በመደመር ዕሳቤ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ጥቅም ንጥልም ቀላልም አይደለም፤ በተለያዩ ዐውዶች ገዝፎ ይገለጣል እንጂ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) እንዳሉት፤ አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብልጽግናን አሠናሥሎ የሚያረጋግጥ ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ነው። የደን፣ የሰብልና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ወሳኝ የልማት አቅጣጫም ነው።

ከችግኝ ተከላ የላቀው የአረጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ

የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ መነሻ፤ የተራቆተ አካባቢን ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ከማድረግ የላቀ ድርብርብ ግብ ያለው ሰፊ መርሐ-ግብር ነው።

በዚህም መሠረት፤ እንደየ ሥነ-ምኅዳሩ የሚላመዱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላላቸው ችግኞች፣ ለደን ሽፋን ማደግ የጎላ ሚና ለሚኖራቸው ችግኞች፣ ለከተማ ውበትና ለማረፊያ ጥላ ለሚሆኑ ዛፎች፣ መሬትን ቆንጥጦ በመያዝ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የሚችሉ ዛፎች የሚተከሉበት ነው።

ይህም አንድን አካባቢ አረንጓዴ ከማድረግ ልቆ በረሃማነትን በመቀነስ፣ የዓየር ንብረት ተጽዕኖን በመቀነስ፣ ምርታማነትን በመጨመር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ነው። የአካባቢ መጎዳት የሚያስከትለው ቀውስና የተፈጥሮ አደጋ በመላው ዓለም በስፋት እየታየ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሐሳብ አመንጭነትና ቁርጠኛ አመራር ሰጭነት ባለፉት ዓመታት በብርቱዎቹ ኢትዮጵያውያን ርብርብ 48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፤ ውጤቱንም ሕዝቡ ዐይቷል።

ከውጤቶቹ መከካልም ለአብነት፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን አሁን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉ፣ የምርታማነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መጨመር ብሎም ውብና አረንጓዴ ከተሞች መስፋፋት የሚሉት ይነሳሉ።

በሕዝቡ ዘንድ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ተፈጥሮን የመንከባከብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የሀገርን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ጭምር ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።

የአረንጓዴ ዐሻራን ውጤት ላጣጣመ ሥራውን በንቃት እንዲከውን መካሪ ባያሻም፤ ካለፈው የበለጠ ውጤት እንዲገኝ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን በነቂስ መሳተፍ ባህል እያደረጉት ይገኛል።

ከአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋቶች መካከል

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (/) ሐሳብ አመንጭነት 2011 . ጅማሮውን ያደረገው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ አሁን ዘርፈ-ብዙ ጥቅሙ በተጨባጭ እየተገለጠ ነው።

ከበርካታ ትሩፋቶቹ መካከልም የምርታማነት ማደግ ተጠቃሽ ነው። ይህን ተከትሎም የሕብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አድጓል። ይህን ሐሳብ በአኃዝ አስደግፈን ብናየው፤ ከአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በፊት (2010 .) በሔክታር የሚመረተው ስንዴ 22 ኩንታል፣ በቆሎ 30 ኩንታል፣ ጤፍ 17 ኩንታል እንዲሁም ገብስ 23 ኩንታል ነበር።

ከኢንሼቲቩ ትግበራ በኋላ ደግሞ (2017 .) ስንዴ በሔክታር 36 ኩንታል፣ በቆሎ 46 ኩንታል፣ ጤፍ 20 ኩንታል፣ ገብስ 30 ኩንታል ማምረት ተችሏል። በዚህም መሠረት 2017 . 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ሔክታር መሬት በስንዴ ሰብል በመሸፈን 280 ሚሊየን ኩንታል ማምረት ተችሏል።

ስንዴን በትጋት በማምረትም ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረን 1 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ተችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በፍራፍሬው ዘርፍ ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል። በዚህም ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ ሕብረተሰቡ (አምራቹ) ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ በዚያው ልክ እንዲያድግ አስችሏል።

ኢትዮጵያም በአፍሪካ አቮካዶን በቀዳሚነት ወደ ውጭ የምትልክ ሁለተኛዋ ሀገር እንድትሆንም አስችሏታል።

ሌላኛው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ትሩፋት የቡና ልማት መስፋፋትና የውጭ ምንዛሬ ማደግ ነው። ይህን በአሥረጂ አስደግፈን ብንመለከት፤ 2011 . 600 ሺህ ሔክታር ላይ ቡና ተተክሏል። 500 ሺህ ሜትሪክ ቶን የቡና ምርት ተሰብስቧል። 738 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

እንዲሁም 2017 . 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ ቡና ተተክሏል። 1 ነጥብ 58 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የቡና ምርት ተሰብስቧል። 2 ነጥብ 65 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢም ማግኘት ተችሏል።

2018 የበጀት ዓመት ደግሞ ወደ ውጪ ከተላከ የቡና ምርት 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

እንዲሁም ከአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ጋር በተያያዘ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ፤ የአካባቢ መራቆትን በመቀነስና በመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል፣ በደን መጨፍጨፍ ምክንያት ይከሰት የነበረን የበረሃማነት መስፋፋት ቀንሷል፣ የደን ሽፋንን ጨምሯል፣ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ መሬት እንዲያገግም በማድረግ ምርታማነትን ጨምሯል።

በተጨማሪም የውኃማ አካላትን መመናመን ቀንሷል (ደርቀው የነበሩ ስፍራዎች ወደ ቀድሞ ውኃማ ይዘታቸው እንዲመለሱ አስችሏል) የአካባቢ መራቆትና የዓየር ንብረት ፈተናዎችን በመቀነስ ረገድም የራሱን ከፍተኛ ሚና አበርክቷል።

ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር በተያያዘ በቀጣይ

የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ የለውጡ መንግሥት ከመጣ ወዲህ ላለፉት ዓመታት በተቀናጀ አግባብ ተመርቷል፤ አሁንም እየተተገበረ ነው። በቀጣይ ደግሞ ኢኒሼቲቩ እንዴት መከናወን እንዳለበት ግቦች ተቀምጠዋል።

በዚህም መሠረት፤ የሕዝብ ባለቤትነትን አጠናክሮ ማስቀጠል (አረንጓዴ ባሕል መገንባት) አማራጭ የኃይል አቅርቦት ሥራዎችን ማስፋትና በደን ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ፣ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያ የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለይቶ በጥናት መመለስ የሚሉት የቀጣይ አቅጣጫዎች ናቸው።

በተጨማሪም፤ ከአረንጓዴ ዐሻራ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የባለድርሻ አካላት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር፣ በክረምት ወራት የሚተከሉ ችግኞችን በበጋ ወራት በአግባቡ መንከባከብ ከቀጣይ አቅጣጫዎች መካከል ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በቢሾፍቱ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

8 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ በሆኑበት በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ወቅት አረንጓዴ ለሆነች ነገ፣ ሁላችንም ተስፋን እንትከል ሲሉ ለሀገሬው ጥሪ አቅርበዋል።

ከላይ የተጠቀሱ ማሳያዎችን (ናሙናዎችን) ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በቀጥታ ለሕዝቡ ጥቅም የቆመ ሰው ተኮር መርሐ-ግብር መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም።

ስለዚህ በቀጣይ ሕብረተሰቡ በመደመር ዕሳቤ በዚህ ኢኒሼቲቭ ላይ ያለጠባቂነት በንቃት የመሳተፍ ልምዱን ማሳደግ አለበት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም