ቀጥታ፡

በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ62 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይተከላሉ

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 26/2018(ኢዜአ)፦በወላይታ ዞን በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ62 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዘማች ሶርሳ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ በተጀመረው የዘንድሮው የክረምት ወራት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ62 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይተከላሉ። 

እንዲሁም በመርሃ ግብሩ ከ105 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ፣ የቡና እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል። 

በዞኑ መርሃ ግብሩ የመሬት ለምነትን በመመለስና የጠፉ ምንጮች እንዲፈልቁ በማድረግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን ማስገኘቱን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። 

በዚህም ሁሉም የዞኑ ማህበረሰብ በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ላይ ያለውን ተሳትፎ በማጠናከርና አሻራውን በማሳረፍ፣ ለነገው ትውልድ ውብና ለምለም አካባቢን የማስረከብ ትልምን ለማሳካት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።

በዞኑ በጠበላ ከተማ የአላታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለሙ ኦሳ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ የአካባቢያቸው ስነ-ምህዳር መሻሻሉን ገልጸዋል። 


 

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተገኘውን ዘርፈ ብዙ ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ችግኞችን መትከልና መንከባከብን ባህል አድርገው እየከወኑት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

"ችግኝ መትከል ከጀመርን ወዲህ የማሳችን ልምላሜ እንዲሁም ምርትና ምርታማነታችን ጨምሯል" ያሉት አርሶ አደሩ፣ ዘንድሮም ይህንን ለውጥ ለማስቀጠል የቡና፣ የፍራፍሬ እና ሌሎችንም ችግኞችን በስፋት እየተከሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዞኑ በሁምቦ ወረዳ የሾጮራ ኦጎዳማ ቀበሌ አርሶ አደር ሳፈነ ሻንካ እና በለጠ በርገነ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ ዛፎችን በብዛት በመቁረጣቸው አካባቢያቸው ተራቁቶ በድርቅና በረሃብ ሲጎዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። 


 

መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ ግን ለምግብነት፣ ለገበያ የሚሆኑና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከላቸው ስነ-ምህዳሩ ተሻሽሎ ዝናብ በወቅቱ እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጠፍተው የነበሩ ምንጮች እየፈለቁና ለእንስሳትም በቂ መኖ ማግኘት መጀመራቸውን አንስተዋል። 

በመሆኑም የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል በተከላውም ሆነ በእንክብካቤው ስራ ላይ ሳንታክት እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም