ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ወጭ ንግድ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኘች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ወጭ ንግድ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኘች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ወጭ ንግድ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙኅን በሰጡት መግለጫ፤ በበጀት ዓመቱ ከቡና ወጪ ንግድ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት የታቀደው ግብ ሙሉ በሙሉ መሳካቱን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ወጪ ንግድ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቷም ሁሉም ባለድርሻ አካል ለቡና ምርታማነት ዕድገት ትኩረት በመስጠቱ የመጣ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ወጪ ንግድ ስኬትም ዓለም አቀፍ ተፅዕኖን ጭምር በመቋቋም የመጣ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የአስራ አምስት ዓመቱ የቡና ልማት ስትራቴጂም የምርት ጥራትና የዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነትን በማሻሻል እ.ኤ.አ በ2026 ሶስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት አስችሏል ብለዋል።
የገበያ ሥርዓቱን ሪፎርም በማድረግና አሰራርን በማቀላጠፍ፣ የኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን በመቀነስና በመቆጣጠር ጭምር የገቢ አቅምን ማሳደግ እየተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
የቡና ልማትና የገበያው ሰንሰለት በዲጂታል ሥርዓት የታገዘ አሰራር በመዘርጋት የምርት ብክነትና የኮንትሮባንድ ንግድን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደተቻለ አስረድተዋል።
ውስን የነበረውን የቡና ምርት የገበያ መዳረሻ ከ66 በላይ ሀገራት በማሳደግ የኢትዮጵያን ቡና የገበያ ዕድሎች በማመቻቸት ለውጭ ምንዛሬ ገቢ እመርታዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ወጪ ንግድ ከፍተኛውን የገቢ አቅም እንድታገኝ አስተዋፅኦ ለነበራቸው አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።