ቀጥታ፡

በምክር ቤቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች የውክልና ተሳትፎ ማደግ በሃሳብ ክርክር ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት ወሳኝ ነው

አሶሳ፤ ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፡- በምክር ቤቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች የውክልና ተሳትፎ ማደግ በሃሳብ ክርክር ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ላለፉት በርካታ ዓመታት በአንድ ገዥ ፓርቲ ፍጹም ቁጥጥር ስር የነበረና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና እጅግ የተገደበ የነበረበት መሆኑ ይታወቃል። 

በሀገሪቱ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ በተካሄዱት ጠቅላላ ምርጫዎች ግን፣ የምርጫ ሥርዓቱን ነጻ፣ ገለልተኛና ታማኝ ለማድረግ በርካታ የህግና የተቋማት ማሻሻያዎች ተደርገዋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ቀደም ባሉት ምርጫዎች የነበረው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎና የህዝብ ውክልና ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም፣ በሂደት በተደረጉ የፖለቲካ ሪፎርሞችና የውይይት መድረኮች ፓርቲዎች በነጻነት የመንቀሳቀስና አማራጭ ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ የማቅረብ ዕድላቸው እያደገ መጥቷል።

ይህ ውጤት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ የህዝብ ድምፅ አግኝተው የፖለቲካ ሥልጣን መጋራትና አማራጭ ሃሳብን ማሰማት የሚችሉበት ምህዳር እየተፈጠረ መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም የብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በመያዝ ያሸነፈ ሲሆን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ከበፊቱ የተሻለ የክልል ምክርቤት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አግኝተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንደተናገሩት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ምህዳር እያደገ መምጣቱ የታየበት ነው።

የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ /ቤሕነን/ ፓርቲ ሊቀመንበር አብዱሰላም ሸንገል፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነበረው የፖለቲካ ተሳትፎ ሀሳብ ብቻ ገዢ እና አሸናፊ የሆነበት ነው ብለዋል።

ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ አካታች የሆነ  የፖለቲካ ትርክትን መከተል እንደሚያስፈልግ ገልፀው፥ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሁሉም መስክ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ በአሸናፊው የብልጽግና ፓርቲ የሚመሠረተው መንግሥት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ታሳቢ ማድረግ እንዳለበትና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከመንግስት ጋር አብረው ለመስራት ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲዳብር የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ፓርቲያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ማግኘቱን የተናገሩት አቶ አብዱሰላም፤ ከክልሉ መንግስት ጋር የጀመሩትን ትብብር በማጠናከር ለክልሉ ሰላምና ልማት በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ጉሕዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ለሜሳ ኔኖ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ባገኘው መቀመጫ ከመንግሥት ጋር የበለጠ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን  ገልጸዋል።

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥትም የሁሉንም ህዝብ ድምጽ በመስማትና የበለጠ ሀገራዊ ሀላፊነት እንደተረከበ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሙሉ ቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም