መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም አሳድጓል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና እያደረገ ያለው ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉን የተለያዩ አምራቾች ገለጹ።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የማምረትና የአምራች ኢንዱስትሪ አቅምን በማሳደግ የወጪ ንግድ እንዲስፋፋና የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲጨምር እያደረገ ነው፡፡ ስትራቴጂው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን በማዳን ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት በማጠናከር ለሀገር በቀል ኢኮኖሚው ስኬትና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው አምራቾች የማምረት አቅማቸው በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን፣ የወጪ ንግድን ማስፋፋታቸውንና የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ትልቅ ስኬት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
የቢጂአይ (BGI) ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ሶሉሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርታ ገላናው እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ባሳለፋቸው ከ17 በላይ ዓመታት ውስጥ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ድርጅታቸው የተለያዩ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽነሪዎችን በማምረት በሀገር ውስጥ እየተካ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ከፍተኛ ድጋፍና ማበረታቻ የማምረት አቅማቸው እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ በመንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ ተወዳዳሪነቱ እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ከ200 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
የሌጀንድ ኢንዱስትሪያል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሹሜ ሆርዶፋ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ተኪ ምርትን በማምረት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የተለያዩ አልባሳትን፣ የተማሪዎች ዩኒፎርሞችን እንዲሁም የአውቶቡስ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ዩኒፎርሞችን እያመረተ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግሥት ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል የመሠረተ-ልማት ችግሮች በመቀረፋቸው፣ ድርጅቱ የማምረት አቅሙን በማሳደግ ምርቶቹን በጥራትና በፍጥነት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ጠቁመዋል።
ድርጅቱ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ጠቁመዋል።
በፋብሪካዎቹ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በበኩላቸው፤ በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሌጀንድ ኢንዱስትሪያል የሥራ ዕድል የተፈጠረላት በላይነሽ ኃይሉ እንዳለችው፤ በፋብሪካው ያገኘችው የሥራ ዕድል ራሷንና ቤተሰቧን የምታስተዳድርበትን ዕድል እንደፈጠረላት ገልጻለች።
በዚሁ ድርጅት ውስጥ የሥራ ዕድል ያገኘው ዮናስ ግዛው በበኩሉ፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ ረገድ ገንቢ ሚና እንዳለው ተናግሯል።
በቢጂአይ ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ሶሉሽን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ኡመር ሁሴን በበኩሉ፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመስፋፋታቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን መቻሉን ገልጾ፣ ይህም የሥራ ባህሉን ይበልጥ እንዲያዳብር እንዳስቻለው ተናግሯል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በሰጡት ሐሳብ፤ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድገት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪዎችን አነስተኛ የማምረት አቅም በማሳደግም ትልልቅ ለውጦችና ስኬቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።
በቀጣይም ለዘርፉ ዕድገትና ውጤታማነት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።