ቀጥታ፡

በአረንጓዴ አሻራ ቋሚ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ሕይወታችንን በመለወጥ ላይ እንገኛለን

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፡- በአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ቋሚ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ሕይወታችንን በመቀየር ላይ እንገኛለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሴቶች ገለጹ፡፡ 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም. በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ እና አስደማሚ አሻራ ማኖር ተችሏል፡፡

በተያዘው ዓመትም 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃም ባለፉት ሰባት ዓመታት 90 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ ሽፋኑን እጅግ ዝቅተኛ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ማድረስ ተችሏል ።

በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ ለብሰዋል፤ የነጠፉ ወንዞች እና አካባቢዎች ማንሰራራት የቻሉ ሲሆን አዲስ አበባን ንፁህ፣ ውብ፣ ለመኖር ምቹ እና የቱሪስት ማዕከል መሆን ችላለች። 

በዚህ ዓመት በከተማ ደረጃ ስድስት ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የማስመጀሪያ መርሐ ግብር ተከናውኖ የተከላ ሂደት ተጀምሯል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ችግኝ በማፍላት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች በመርኃ-ግብሩ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ኑሯቸውን በማሻሻል ላይ ይገኛሉ፡፡

በችግኝ ማፍላት ሥራ ላይ የተሰማራችው አበበች ተካ፣ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚውሉ ችግኞችን በማፍላትና በማቅረብ ቋሚ ሥራና አስተማማኝ ገቢ በማግኘት ላይ መሆኗን ጠቅሳለች፡፡

በዚህም ኑሮዋን በበጎ ሁኔታ በመምራት ላይ እንደምትገኝ ገልጻለች። 


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ራሔል ዮሐንስ በበኩሏ፤ በችግኝ ጣቢያ ውስጥ ያገኘችው ሥራ ገቢ አግኝታ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንድትላቀቅና ከራሷ አልፋ ቤተሰቦቿን መደገፍ እንድትችል ማድረጉን ጠቅሳለች፡፡

ችግኞችን መንከባከብ ለአካላዊና መንፈሳዊ ጤንነቷ ከፍተኛ አዎንታዊ ስሜት እንደሚፈጥርላት ተናግራለች።

ለበርካታ ዓመታት በአረብ ሀገር በስደት ቆይታ ወደ ሀገሯ የተመለሰችው ሐና ማሞ እንዳለችውም፤ በሀገር ላይ ሠርቶ ከመለወጥ የበለጠ ደስታና ዓለም እንደሌለ ትናገራለች። 


 

ወደ ሀገሯ በመመለስ በተፈጠረላት የሥራ ዕድል በቋሚነት ችግኝ በማፍላትና በማቅረብ ሥራ ላይ መሰማራቷን ጠቅሳ፤ ሀገርን የሚጠቅም ሥራ እየሠራች ራሷም ተጠቃሚ መሆን መቻሏ ልዩ ደስታ እንደፈጠረላት አመልክታለች። 

በዚህም በችግኝ ጣቢያ ማዕከል ውስጥ ሥራ በመሥራት ራሷንና ቤተሰቧን በመደገፍ ኑሮዋን በበጎ ሁኔታ በመመስረት ላይ መሆኗን ገልጻለች።


 

የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የአረንጓዴ ቦታዎች አያያዝ፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አጥናፉ ፤ በዘንድሮው የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ የሆኑ በርካታ የፍራፍሬና ሌሎች ሀገር በቀል ዝርያ ያላቸው ችግኞች በስፋት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ቢሮው በችግኝ ማፍላት ሥራ ላይ ብቻ ከአራት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም