ቀጥታ፡

አረንጓዴ ዐሻራ የሥርዓተ ምህዳር ደህንነትን በማስተካከል ለዱር እንስሳት ሀብት ጥበቃ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

አዲስ አበባ ፤ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦አረንጓዴ ዐሻራ የአካባቢ ሥርዓተ ምህዳር ደህንነትን በማስተካከል ለዱር እንስሳት ሀብት ጥበቃ ምቹ  ሁኔታ መፍጠሩን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጂራ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ባለፉት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮች ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ተክላለች። በዚህም የአገሪቱ የደን ሽፋን ከ17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሏል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጂራ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለዱር እንስሳት ሀብቶች መጠበቅ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የዱር እንስሳት ሀብቶቻችንን ጠብቆ ለማቆየት ምቹ አካባቢን መፍጠር ይገባናል ብለዋል።

ልዩ ልዩ የዱር እንስሳት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ የሚኖሩበትን የደን ስፍራ ከተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች መከላከል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።


 

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መተግበር ከጀመረ ወዲህ የተራቆቱ መሬቶችን ወደ ተፈጥሯዊ ሥነ ምህዳር በመመለስ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን በመግለጽ፤ ይህም ለዱር እንስሳት ተስማሚ የአካባቢ ሥርዓተ ምህዳር ፈጥሯል ብለዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የእጽዋት ሽፋን በጨመረባቸው አካባቢዎች፤ የአእዋፋት እና የዱር እንስሳት ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን አክለዋል።

ለአብነትም በአቢጃታ-ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ የቆላ አጋዘንን ጨምሮ ሌሎች የዱር እንስሳትን በስፋት ማየት የተቻለበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የሐይቁ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን አስታውሰው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ትግበራ የሐይቁን የውኃና የመልክዓ ምድር ስፋት እንዲጨምር ማድረጉንና አእዋፋት በስፋት የሚታዩበትን ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይ ሁኔታ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተደጋጋሚ የደን ቃጠሎ የሚታይበት እንደነበረ አስታውሰው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መጀመሩ ጉዳቱን ለመቀነስ ትልቅ አቅም መፍጠሩን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

በዚህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው 8 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም