ቀጥታ፡

በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚመከርባቸው ዐበይት አጀንዳዎች ጠንካራ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችሉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚመከርባቸው አሳታፊና አካታች ዐበይት አጀንዳዎች ጠንካራ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን በስልጡን የምክክር መፍትሔ ለመስጠት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ለዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተሰናድተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ከሚቀጥለው ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚያካሂደው ዋናው ሀገራዊ ጉባኤም ስምንት ዐበይት አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

በአጀንዳዎቹም የሀገር ግንባታ፣ የመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባና ድሬዳዋ ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስናና መልካም አስተዳደርና ሰላም ግንባታ ናቸው።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉትም፤ የሀገራዊ ምክክሩ ስምንት የዋናው ጉባኤ የምክክር ዐበይት አጀንዳዎች የኢትዮጵያን ወሳኝ ጉዳዮች የያዙ ናቸው።

ሀገራዊ ምክክሩም በዜጎች መካከል ለዘመናት የሚነሱ የአለመግባባት ሃሳቦችን በምክክር በመፍታት በሁሉም መስክ የጋራ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አቅም መገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎች መካከል መቶ አለቃ ጋዲሳ አብዲ፤ የሀገራዊ ምክክሩ የህዝብ አሳታፊና አካታችነት በዜጎች መካከል ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባት ወሳኝ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የዋናው ጉባኤ ቁልፍ አጀንዳዎችም የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት በማስቀጠል በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።


 

ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ገዛኸኝ ደሜ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ የዘመናት ቅራኔን በውይይትና ስምምነት መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።

በዋናው ጉባኤ የሚመከርባቸው ስምንቱ ዐበይት አጀንዳዎችም የህዝብን ፍላጎቶችና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማሸጋገር እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ የህዝብ ተሳትፎና አካታችነት በመሰረታዊ የልማትና ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መግባባትን በመፍጠር የጋራ ዕድገትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ለማ ወተሬ ናቸው።


 

በዋናው የምክክር ጉባኤ የሚመክሩ የህዝብ ወኪሎችም ስልጡን ምክክር በማድረግ ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅሙ መፍትሔዎችን ማፍለቅ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ወጣት ክብሬ አባረዳ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር በጋራ አስተሳሰብና ፍላጎት የምትገነባ ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ መሰረት ይጥላል ብሏል።


 

በዐበይት አጀንዳነት የሚመከርባቸው ጉዳዮችም ከህዝብ የመነጩና ለሀገራዊ ዕድገትና ሰላም መግባባትን ለመገንባት የሚበጁ መሆናቸውን ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም