የምክክር አጀንዳዎቹ የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ጠንካራ አንድነትን ለመፍጠር ወሳኝ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር አጀንዳዎቹ የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ጠንካራ አንድነትን ለመፍጠር ወሳኝ ናቸው
ቦንጋ፤ ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ):-ለዋናው የምክክር ጉባኤ የተለዩ አጀንዳዎች የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና መግባባትን ለመፍጠር ሚናቸው የላቀ መሆኑን የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ መምህራን ገለፁ።
በሀገሪቱ ዘመናትን ያስቆጠሩ አለመግባባቶች በውይይት ለመፍታት ቁልፍ መሳሪያ የሆነው ሀገራዊ ምክክር በርካታ ሂደቶችን አልፎ ወደመቋጫው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓም በሚያካሂደው ዋናው የምክክር ጉባኤም ምክክር የሚደረግባቸውን ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ለይቶ ይፋ አድርጓል።
ተደራጅተው በቀረቡ የምክክር አጀንዳዎች ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ምሁራን በኮሚሽኑ የተለዩ አጀንዳዎች ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ዋና ዋና ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና መግባባትን ለመፍጠር ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኮሌጁ የስነዜጋ እና ስነምግባር ትምህርት ክፍል መምህር እንግዳ ገብረማርያም እንደገለጹት፣ ችግሮችን በውይይትና በምክክር መፍታት የስልጣኔ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሸን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሰባሰባቸውና አደራጅቶ ያቀረባቸው የምክክር አጀንዳዎች ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችሉ ናቸው።
ይህም ለዘመናት ለቅራኔ ምንጭ የነበሩና የማያግባቡ ችግሮች በመፍታት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ የሁሉንም አካባቢዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ አጀንዳዎችን ለይቶ ማቅረቡ የሚደነቅ መሆኑን ያነሱት መምህር እንግዳ፣ ብዙ ውጣውረዶችን ያለፈው ምክክር ስኬታማ እንዲሆን የሁሉም አስተዋጾ ያስፈልጋል ብለዋል።
በኮሌጁ የጂኦግራፊና የአካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር አለማው ብሩ በበኩላቸው፣ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታትን ባህል ማድረግ ለጠንካራ ሀገረ መንግት ግንባታ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል።
እንደሀገር ባለፉት ዘመናት የተፈጠሩ ልዩነቶችን በውይይትና በምክክር ለመፍታት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ብዙ ሂደቶችን አልፎ ወደመቋጫ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አድንቀው፣ ምክክሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ታሪካዊ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም ይገባናል ብለዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የነቃ ተሳትፎ በማድረግና ይህን ወርቃማ ዕድል ወደውጤት መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የሀገረ መንግስት ግንባታ፣ የመንግስት አደረጃጀት እና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርአት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሂደት፣ የፌደራል ከተሞች (አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ድሬዳዋ አስተዳደር) ጉዳይ የሐይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የህግ የበላይነት ለዋናው ጉባኤ ከተለዩ አጀንዳዎች መካከል ይገኙበታል።
በተጨማሪም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች፣ ሙስና እና መልካም አስተዳደር፣ ሰብአዊ መብቶች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ምክክር የሚደረግባቸው ነጥቦች መሆናቸውም መገለጹ ይታወሳል።