የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ወደ ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ወደ ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ገቡ
አዲስ አበባ ፤ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ያቀፈ ከፍተኛ የዲፕሎማቶች ልዑክ የዓለም ቅርስ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጎብኘት ዛሬ ወደ ታሪካዊቷ ከተማ ገብተዋል።
የዲፕሎማቲክ ልዑኩ አባላት ላሊበላ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ፣ የአካባቢው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ጉብኝቱ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት መሰረት ቅርሶችን እና ታሪካዊ ቦታዎችን በአግባቡ በመጠበቅ፣ በማልማትና ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ ስራዎችን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።
የልዑኩ አባላት በቆይታቸው በዩኔስኮ የተመዘገቡትን ድንቅ የውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥበብና መንፈሳዊ ድባብ በአካል ተገኝተው የሚመለከቱ ይሆናል።
ይህ ጉብኝት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ፣ አስደናቂ የስነ-ህንጻ ጥበብ እና የባህል እሴቶችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይበልጥ ለማስተዋወቅ እንዲሁም የሀገሪቱን የባህል ዲፕሎማሲ እና የቱሪዝም ዘርፍ ለማጠናከር ትልቅ ሚና ይኖረዋል።