የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሰላምና ዕድገት የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት መሰረት የሚጥል ነው - የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሰላምና ዕድገት የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት መሰረት የሚጥል ነው - የኃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ ፤ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የዜጎችን ጠንካራ የአብሮነት ዕሴት በሀገራዊ መግባባት በማፅናት ሰላምና ዕድገት የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑን የኃይማኖት አባቶች ገለጹ።
ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን በስልጡን የምክክር መፍትሔ ለመስጠት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ መድረክ ማካሄዱ ይታወቃል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሚቀጥለው ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚያካሂደው ዋናው ሀገራዊ ጉባኤም ስምንት ዐበይት አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።
በአጀንዳዎቹም የሀገር ግንባታ፣ የመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባና ድሬዳዋ ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስናና መልካም አስተዳደር እና ሰላም ግንባታ ተካተዋል።
የኃይማኖት አባቶች ለኢዜአ እንዳሉትም፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የዜጎችን ጠንካራ የአብሮነት ዕሴት ሀገራዊ መግባባት በማፅናት ሰላምና ዕድገት የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት መሰረት የሚጥል ነው።
የኃይማኖት ተቋማት በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር ምዕራፎች ያደረጉትን ንቁ ተሳትፎ በዋናው ሀገራዊ ጉባኤም እንደሚያስቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መንበረ ፓትርያክ የጥናትና ምርምር ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል፤ ምክክር በኃይማኖታዊ አስተምህሮ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም ዘመናት የዘለቁ ሀገራዊ ቅራኔዎችን በሰለጠነ አካሄድ መፍትሔ በመስጠት ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥር አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።
ዜጎችም ሀገራዊ ምክክሩ የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም የሰለጠነች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል የምክክር ዕሴትና ባህል ማጎልበት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባል ኢብራሂም ሙሉሸዋ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ የታሪክ ስብራትን የሚጠግንና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ስልጡን የምክክር ባህል ሊጎለብት ይገባል ብለዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት የዘለቁ ቁርሾዎችን በሀገራዊ መግባባት መፍትሔ በመስጠት ዘላቂ ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግናን ለማስቀጠል እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።
ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሰበሰቡ አጀንዳዎች ላይ በመምከር መፍትሔ ለማበጀትም ሁሉም ዜጋ በዋናው ጉባኤ ንቁ ተሳታፎ በማድረግ ለሀገራዊ መግባባት መሰረት መጣል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ መሱድ አደም፤ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋናው ጉባኤ የተሻለችን ሀገር ለትወልዱ ለማስተላለፍ ኃላፊነታችን የምንወጣበት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያናት ካውንስል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር መጋቢ አሸብር ከተማ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያዊያንን አስተሳሳሪ ገመድ በሀገራዊ ምክክሩ ማፅናትና ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም የዘመናት ቁርሾን በሀገራዊ መግባባት በመተካት ለቀጣዩ ትውልድ አዲስ ምዕራፍና ተስፋን የሰነቀ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።