ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ ለከተሞች ውበትና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ተጨማሪ አቅም እየሆነ ነው

ጅማ፤ ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፡- አረንጓዴ አሻራ ለከተሞች ውበት ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሥራ ዕድልን ለማስፋት ተጨማሪ አቅም መሆኑን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ በይፋ ከተጀመረበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን  በአየር ንብረት፣ በምግብ ዋስትና፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ  የማህበረሰቡን የደን ልማትና እንክብካቤ ግንዛቤ ከማሳደጉም በላይ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ጌትነት ሰይድ፤ መርሃ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥንና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ማስቻሉን ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ ከበጋው ወቅት አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ጋር መተሳሰሩም የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃ ሀብት እንዲጎለብት በማድረግ ለመስኖ ልማት ተጨማሪ አቅም መሆኑን አስረድተዋል። 

ለምግብነት የሚውሉ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመው፤ የሚተከሉ ችግኞች ከየአካባቢው ሥነ-ምህዳር እና የአየር ንብረት ሁኔታ ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ የባለሙያዎችና የተመራማሪዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን አክለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጥበቡ አለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የማህበረሰቡን የአካባቢ ጥበቃ ባህል ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል። 

ይህም የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙና የደረቁ ምንጮችን በመመለስ ለብዝሃ ሕይወት መጠበቅ ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የሚተከሉት ችግኞች ሀገር በቀል መሆናቸው የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር ተቋቁመው ለመጽደቅ እንዳስቻላቸው የገለጹት ዶክተር ጥበቡ፤ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በመንከባከብ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታውን ለማጉላት የሁሉም አካላት ርብርብና ድርሻ ያስፈልጋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም