የኮሪደር ልማቱ ሆሳዕናን ለኮንፈረንስ ቱሪዝምና ለነዋሪዎቿ ምቹ እያደረጋት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱ ሆሳዕናን ለኮንፈረንስ ቱሪዝምና ለነዋሪዎቿ ምቹ እያደረጋት ነው
ሆሳዕና፤ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በሆሳዕና ከተማ እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ፅዱ ከማድረግ ባለፈ ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እያደረጋት መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ።
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ተግባራዊ መሆን ከጀመሩ ወዲህ በከተማ ገጽታ፣ በነዋሪዎች ማህበራዊ ህይወት እና በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ እና ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል።
በዚህም ጠባብ እና የተበላሹ መንገዶች ደረጃቸውን በጠበቁ አስፋልቶች በመተካታቸው የትራፊክ ፍሰቱ እንዲቀላጠፍ መደረጉ፣ የመንገድ መብራቶች መሟላት፣ ነዋሪዎች ከስራ በኋላ የሚዝናኑባቸውና የሚያርፉባቸው ቦታዎች መገንባታቸው፣ ለበርካቶች የስራ ዕድል መፈጠሩና ሌሎች ትሩፋቶችን ማንሳት ይቻላል።
በኮሪደር ልማቱ ለአይን ማራኪ እና ለእንቅስቃሴ ምቹ እየሆኑ ከሚገኙ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው ሆሳዕና ከተማ፤ ልማቱ ሀገር አቀፍ ስብሰባዎችን እንዲሁም ቱሪስቶችን ለመሳብ ትልቅ አቅምን ፈጥሯል።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እንዳደረጋት ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተግባራዊ ከሆነው የ24 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ኮሪደር ልማት ስራ ውስጥ 12 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትሩ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉንም አክለዋል።
መንገዱ የእግረኛ፣ የአካል ጉዳተኛና የብስክሌት መሄጃ የተሰራለት ሲሆን፤ አረንጓዴ ስፍራ፣ ፋውንቴን፣ የመኪና ማቆሚያና ስማርት ፖልን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን ያሟላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ትልልቅ ሆቴሎችን ጨምሮ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመበራከታቸው፣ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንሶች በከተማዋ እንዲካሄዱ ምቹ መደላድል መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ደጉ ከባሞ በበኩላቸው፤ የእድሜዋን ያህል ሳትለማ ለቆየችው ሆሳዕና ከተማ የኮሪደር ልማቱ አዲስ ገጽታ እንዳላበሳትና እድገቷም እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ልማቱ ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለቱሪስቶችም ተመራጭ እያደረጋት በመሆኑ ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ገብረየስ ጡሞሮ እና ወይዘሮ ሀንጬቴ አዲሴ በሰጡት አስተያየት፤ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ለነዋሪው ምቹና ፅዱ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከተማዋ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገሯን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት የ24 ሰዓት ሙሉ ያለስጋት የሚንቀሳቀሱባት ከተማ መሆኗን መስክረዋል።
ኮሪደር ልማቱ ከዚህ ቀደም ከተማዋ በነበረባት የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነት ችግር ምክንያት ያጋጥም የነበረውን የትራፊክ አደጋ መቀነሱን የገለጹት ደግሞ አቶ በየነ ዲሌቦና አቶ ኤርመኮ ቢንጫሞ የተባሉ ነዋሪዎች ናቸው፡፡
በዚህም ከተማዋ ለኑሮ፣ ለመዝናኛና ለቱሪዝም ምቹ ከመሆኗም ባለፈ በልማቱ ለዜጎች ከፍተኛ የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡