ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የኢትዮጵያን የተስፋ ጉዞ የሚወስን ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ነው - ምሁራን

አዲስ አበባ ፤ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦የሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የኢትዮጵያን የተስፋ ጉዞ የሚወስን ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ነው ሲሉ አንጋፋ ምሁራን ገለጹ፡፡  

ዜጎች ለምክክሩ ስኬታማነት እስካሁን ያሳዩትን የነቃ ተሳትፎ ማጠናክር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰኔ 17 ቀን 2018 ለዋናው ሀገራዊ ምክክሩ የሚቀርቡ የተለያዩ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ይፋ አድርጓል፡፡ 

እነኚህም ዋና ዋና የጉባኤው አጀንዳዎችም የሀገር ግንባታ፤ የመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርዓት፤ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ጉዳይ፤ የሃይማኖት ጉዳዮች፤ የተቋማት ግንባታ፤ የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፤ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፤ ሙስናና መልካም አስተዳደር እና ሰላም ግንባታ ናቸው፡፡ 

በእነኚህ ዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያም ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ በሚጀምረው ጉባኤ ምክክር ይካሄድባቸዋል፡፡ 

የሀገራዊ ምክክሩ የእስካሁኑ ጉዞ፤ እውነተኛ አሳታፊነትን፣ ፍፁም ግልጽነትን እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማካተት ስራዎችን በስኬት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ስር የሰደዱ ችግሮች የሚፈቱበት አማራጭ የሌለው ሂደት መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያውያን ከሚያራርቃቸው ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቧቸው እንደሚበልጡ ነው የጠቆሙት፡፡

ይህም ምክክሩ ችግሮችን በሰከነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ልዩ የታሪክ አጋጣሚ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ በመመካከርና በመነጋገር የጋራ ግንዛቤ የሚፈጠርበት ትልቅ መድረክ ነው። 

ይህ ሂደት ኢትዮጵያን በተሟላ ሁኔታ ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ምክክሮቹም ወደ ሀገራዊ መግባባት የሚወስዱ ናቸው ብለዋል፡፡ 

የምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን የተጓዘበት ሂደት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የህዝብ ተሳትፎን ከማረጋገጥ አኳያ የተመዘገበው ስኬት በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪና የህግ ጠበቃው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እየተቀየረ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት እንዳይግባቡ ያደረጓቸውን መሠረታዊ ችግሮች ራሳቸው መፍትሄ እንዲያስቀምጡላቸው በር የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል። 

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ስር የሰደዱ ችግሮችን በጥልቀት መመካከር አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማምጣት ሁነኛ መንገድ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለምክክሩ መሳካት ወጣቶችና ምሁራን እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በባለቤትነትና በሃላፊነት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡  

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም