በመዲናዋ የአካባቢ ጥበቃን ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር ያቀናጀ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እየተጠናከረ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የአካባቢ ጥበቃን ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር ያቀናጀ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እየተጠናከረ መጥቷል
አዲስ አበባ ፤ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃን ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር ያቀናጀ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የከተማዋ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሰራተኞችና የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ዛሬ ማለዳ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቦሌ ቡልቡላ ፓርክ ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
ምክትል ከንቲባው አቶ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የተተገበሩና እየተተገበሩ የሚገኙ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች የመዲናዋን ገጽታ፣ የነዋሪዎችን ህይወትና የኢኮኖሚ ግንባታን እያረጋገጡ ነው።
ቀደም ሲል ክፍት እና የቆሻሻ መጣያ የነበሩ ስፍራዎች አሁን ላይ ወደ አረንጓዴነት ተቀይረው ውብ እና አዲስ እየሆኑ መምጣታቸውንም አብራርተዋል።
እነዚህ ስፍራዎች ለከተማዋ ነዋሪዎች መዝናኛ ከመሆን ባለፈ፣ ለውጭ ሀገር ጎብኝዎች የቱሪስት መዳረሻነት እያገለገሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በመዲናዋ በርካታ ችግኞች መተከላቸው የከተማዋን የአየር ንብረት ሚዛን ለመጠበቅ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ከዚህ በፊት ቢሮው በመዲናዋ በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች የራሱን የላቀ ሚና ሲያበረክት መቆየቱን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ በከተማዋ የሚተከሉ ችግኞች ጸድቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማድረግ ረገድም ስኬታማ ተግባር ማከናወኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው ዓመትም ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉ አመራር አባላትን፣ ሰራተኞችንና የኢንዱስትሪ ባለቤቶችን በማስተባበር ልዩ ልዩ ፋይዳ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን ገልጸዋል።
ደኖች ከአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለማስወገድ አይተኬ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊው አቶ ጃንጥራር፤ በመዲናዋ የኢንዱስትሪ ልማትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማጠናከር ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል።