ቀጥታ፡

የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ፦ የወቅቱ ሻምፒዮን አርጀንቲና ከኬፕቨርዴ ጋር የምታደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።

ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ አርጀንቲና ከኬፕቨርዴ በሚያሚ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አርጀንቲና በምድብ 10 በዘጠኝ ነጥብ መሪ ሆና በማጠናቀቅ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።

በዓለም ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ኬፕቨርዴ በምድብ ስምንት በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅለላች።

ከ500 ሺህ በላይ ህዝብ ያላት የደሴቲቷ ሀገር በዓለም ዋንጫው እያሳየች ያለው ብቃት አድናቆት አስችሯታል።

በተለይም በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ከስፔን ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየችበት ውጤት ዓለምን አስገርሟል።

ተጋጣሚዊ አርጀንቲና ሶስት ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያነሳች ሲሆን የወቅቱም የውድድሩ አሸናፊ ናት።

የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ወደ ጥሎ ማለፉ ስትገባ የአሁኑ ለ15ኛ ጊዜ ነው።

የ39 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ በዓለም ዋንጫው ስድስት ግቦችን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል።

በዓለም ዋንጫው በአጠቃላይ ከመረብ ላይ ያሳረፋቸውን ግቦች 19 በማድረስ የውድድሩ የምንጊዜም ከፍተኛ አስቆጣሪ ነው።

በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለቤት አርጀንቲና አንደኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ ኬፕቨርዴ ደግሞ በ64ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በጨዋታው አርጀንቲና የማሸነፉን ከፍተኛ ግምት አግኝታለች።

በጥሩ የራስ መተማመን ላይ የሚገኘው የኬፕቨርዴ ብሔራዊ ቡድን ያልተጠበቀ ውጤት ሊያስመዘግበበት የሚችልበት እድል አለ።




የጨዋታው አሸናፊ ከአውስትራሊያ እና ግብጽ አሸናፊ ጋር በቀጣዩ ዙር ይገናኛል።

‘በሌላኛው መርሐ ግብር ኮሎምቢያ ከጋና በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ከ30 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኮሎምቢያ በምድብ 11 በሰባት ነጥብ በመሪነት በማጠናቀቅ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።

ጋና በምድብ 12 በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ በምርጥ ሶስተኝነት 32ቱን ተቀላቅላለች።

ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ኮሎምቢያ ለአራተኛ ጊዜ፣ ጋና ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ማለፍ ምዕራፍ መሸጋገር ችለዋል።




የጨዋታው አሸናፊ 16 ውስጥ ከስዊዘርላንድ ጋር ይገናኛል። 

አውስትራሊያ ከግብጽ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ በዳላስ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አውስትራሊያ በምድብ አራት በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ወደ ጥሎ ማለፉም ለሶስተኛ ጊዜ አልፋለች።

በምድብ ሰባት የነበረችው ግብጽ በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።

ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ግብጽ አንድ ጊዜ ስታሸንፍ ቀሪው መርሐ ግብር በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም