ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩት የሚያሰራጨው የአየር ትንበያ መረጃ ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል

ሮቤ፤ ሰኔ 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚያሰራጨው የአየር ትንበያ መረጃ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስገኝ ባለድርሻ አካላትና ተጠቃሚው ማህበረሰብ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ።

የደቡብ ኦሮሚያ የሜቲዎሮሎጂ አገልግሎት የበልግ አየር ሁኔታ ትንበያ ግምገማና የመጪው ክረምት የአየር ትንበያ የምክክር መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሮቤ ከተማ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የደቡብ ኦሮሚያ ሜቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሙላቱ ወርቅነህ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ ኢንስቲትዩቱ የአየር ትንበያ አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።


 

የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎቶችን ይበልጥ ማስፋትና ማዘመን ከእውነታ ጋር የተቀራረበ የአየር ትንበያ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

አቶ ሙላቱ እንዳሉት፤ ማዕከሉ በደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በቀጣይ የክረምት ወቅት የዝናብ ሁኔታ 20 በመቶ ከመደበኛ በላይ፣ 45 በመቶ መደበኛና 35 በመቶ ከመደበኛ በታች እንደሚሆን መተንበዩን ገልጸዋል።

ባለድርሻ አካላትም በተለይ ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚያገኙ በተተነበዩ አካባቢዎች አርሶ አደሮች ማሳቸውን ፈጥነው በሚደርሱ የሰብል ዓይነቶች እንዲያለሙ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ መክረዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የአገልግሎቱን የአየር ሁኔታ ትንበያ በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ በበኩላቸው ከአገልግሎቱ በየወቅቱ የሚገኘው የአየር ትንበያ መረጃ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀምና ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ደግሞ ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በየጊዜው የሚቀርበው የአየር ትንበያ መረጃ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስኬታማነት እያገዛቸው መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የደቡብ ኦሮሚያ ሜቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ከሚሸፍናቸው አካባቢዎች መካከል የባሌ ዞን፣ ምሥራቅ ባሌ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ከፊል አርሲና ምዕራብ አርሲ ዞኖች እንደሚገኙበት ተመልክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም