ቀጥታ፡

ፖርቹጋል ቀጣዩን ዙር ተቀላቀለች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ32ቱ የጥሎ ማለፍ ተጠባቂ መርሐ ግብር ፖርቹጋል ክሮሺያን 2 ለ 1 አሸንፋለች።

ከእኩለ ሌሊት በኋላ በቶሮንቶ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኢቫን ፔሪሲች በ53ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል ክሮሺያን መሪ አድርጓል።

የ41 ዓመቱ የቡድኑ አምበል ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ68ኛው ደቂቃ የፖርቹጋልን የአቻነት ግብ በፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ ላይ አሳርፏል።

አጥቂው ጎንካሎ ራሞስ በ94ኛው ደቂቃ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ጎል ፖርቹጋል አሸናፊ ሆናለች።

ፖርቹጋል በጨዋታው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ብትወስድም ክሮሺያ ግልጽ የሆኑ የግብ እድሎችን በመፍጠር ተሽላ ተገኝታለች።

የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ሶስት አድርሷል።

በዓለም ዋንጫ ተሳትፎው በጥሎ ማለፍ ምዕራፍ የመጀመሪያ ጎሉን ከመረብ ላይ አሳርፏል።  

በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛትም ወደ 11 ከፍ አድርጓል።

ለፖርቹጋል 146ኛ የብሔራዊ ቡድን ጎሉን ከመረብ ላይ ያሳረፈው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በፕሮፌሽናል ደረጃ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት 976 አድርሷል።

1000 ጎሎች ለመድረስ 24 ግቦች ይቀሩታል።

ውጤቱን ተከትሎ ፖርቹጋል 16ቱን የተቀላቀለች ሲሆን ከስፔን ጋር በቀጣዩ ዙር የምታደርገው ጨዋታ ከወዲሁ ይጠበቃል።

ክሮሺያ የዓለም ዋንጫ ጉዟዋ ብዙም ርቀት ሳትሄድ ተገቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም