ኢትዮጵያ ለስደተኞች ምቹ ምኅዳር በመፍጠርና ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ የተግባር ምሳሌ ናት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለስደተኞች ምቹ ምኅዳር በመፍጠርና ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ የተግባር ምሳሌ ናት
አዲስ አበባ፣ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለስደተኞች ምቹ ምኅዳር በመፍጠርና ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ የተግባር ምሳሌ ናት ሲል የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ከዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅትና ከኔዘርላንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ለስደተኞችና ተቀባይ ማህበረሰብ የሥራ ላይ ልምምድና የሥራ ቅጥር አውደ ርዕይ አካሂዷል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብሩህተስፋ ሙሉጌታ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን በመቀበል ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠ ይገኛል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች በመተግበር ስደተኞች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ምቹ ምኅዳር መፍጠሯን ገልጸዋል።
የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት የኢትዮጵያና የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ኩምቡላ ንዳባ በበኩላቸው፤ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለፈጠራና ስራ ዕድል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
አውደ ርዕዩ ወጣቶችን ከቀጣሪዎች ጋር የሚያገናኝ ብሎም ስደተኞችንና ተቀባይ ማህበረሰብን ተሳታፊ በማድረግ አካታችነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ክሪስቲን ፒሬን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ይፋ ያደረገው የማካተት ፍኖተ ካርታ የስደተኞችን አካታችነት የሚያረጋግጥ ቁርጠኛ እርምጃ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በለጠ እሱባለው፤ ዓውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የዲጂታል ኢኮኖሚ ምቹ የሥራ ዕድሎችን እና ተግባራዊ ልምምዶችን ለማስፋት ያለመ መሆኑን ገልፀዋል ።
ዓውደ ርዕይ በኢንዱስትሪው፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በመንግስት መካከል ያለውን የሶስትዮሽ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ፓርኩ በ2030 የአፍሪካ ተመራጭ የዲጂታል ፈጠራ ማዕከል ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ለዚህም በፓርኩ ውስጥ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ የቴሌኮም ኦፕሬተሮችና የዳታ ማዕከላት ተገንብተው የዜጎችን የዲጂታል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል።