ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ግንኙነት በሁሉም መስክ ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው - አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር

አዲስ አበባ፣ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ግንኙነት በሁሉም መስክ ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር ገለጹ።

አምባሳደር ሶፊ ኢመስበርገር ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ታሪካዊ ግንኙነት ስኬታማ የትብብር ዕድገት እያስመዘገበ ነው።

ለአብነትም ከወራት በፊት የኢትዮ-አውሮፓ የንግድ ፎረም በርካታ የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኩባንያዎች በተሳተፉበት በፈረንሳይ ፓሪስና በአዲስ አበባ መካሄዱን አስረድተዋል።

ፎረሙ የኢትዮ-አውሮፓን የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ወሳኝ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ወደ አውሮፓ ለመጓዝ የቪዛ ማመልከቻቸውን ከ45 ቀናት በፊት ማስገባት እንዳለባቸው የሚደነግገው የቪዛ ገደብ መነሳቱም የንግድና የባህል ግንኙነትን እያጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት፣ ዲጂታላይዜሽን፣ አግሮ-ኢንዱስትሪና የጤና ጥበቃ ስኬቶችም ከአውሮፓ ሕብረት የልማት መርሃ ግብር ጋር በእጅጉ የሚጣጣም መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም በኢትዮጵያ የሚደረጉ የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንቶችን ለማበረታታትና ለመደገፍም ህብረቱ ባስጀመረው የግሎባል ጌትዌይ ማዕቀፍ እየተሰራበት መሆኑን አስረድተዋል።

የአውሮፓ ህብረት፣ ፈረንሳይ እና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር በሀገሪቱ ያለውን የኤሌክትሪክ እና የዲጂታል መሰረተ-ልማትን ለማዘመን የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል።

የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራትና የኢትዮጵያ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት በትምህርትና በምርምር ዘርፍ ጭምር ትልቅ ፍሬ እያፈራ መሆኑን አስረድተዋል።

የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ግንኙነትና የእርስ በእርስ ጉብኝቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱም የትብብር አድማሱን ወደላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አውሮፓ ከተሞች የሚያደርገው በረራ ትስስሩን እያሰፋ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያና አውሮፓ የረጅም ዘመን ትብብራቸውን እ.አ.አ ከ2016 ጀምሮ ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ያሳደጉ ሲሆን፥ በሁሉም መስክ የላቀ ትብብርን ለመፍጠር ህብረቱ በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም