ቀጥታ፡

ፓርቲዎች ለምክክሩ ስኬታማነት እያበረከቱ የሚገኘውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2018(ኢዜአ)፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምክክሩ ስኬታማነት እያበረከቱ ያለውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስገነዘበ።

የጋራ ምክር ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አድርጓል።


 

በውይይቱ ላይ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈሰ፣ የጋራ ምክር ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርበው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ መስራት እንዲችሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እለት እና በድህረ ምርጫ ወቅት በተቀናጀ መልኩ የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ይህ በጎ ጅምር የበለጠ እንዲጠናከር እና ለሀገረ መንግስት ግንባታው በጎ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በጋራ መቆም ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም በጋራ ምክር ቤቱ ስር የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ድርሻቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ላይ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የጋራ ምክር ቤቱ ጸሐፊ አቶ ታሪኩ ድምበሩ በበጀት ዓመቱ መደበኛ ውይይቶችን በአግባቡ በማካሄድ በፓርቲዎቹ መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከሩን ገልጸዋል።


 

ይህም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ እና አካታች በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው ተናግረዋል።

ይህ በጎ ጅምር በቀጣይ በብሔራዊ ጥቅም እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመቆም የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልን ለማዳበር ያግዛል ሲሉም ገልጸዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ በ2019 በጀት ዓመት አደረጃጀቱን የበለጠ በማጠናከር ሰላማዊ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር ሚናውን ያጠናክራል ያሉት ደግሞ የበጀት ዓመቱን የትኩረት አቅጣጫ ያቀረቡት የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ኢደኤ ናቸው።


 

በአዲሱ በጀት ዓመት ምክር ቤቱ እስከ ዞንና ወረዳ ድረስ ያደራጀው መዋቅር ውጤታማ በሆነ መልኩ ስራውን እንዲሰራ ይደረጋል ነው ያሉት።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የጋራ ምክር ቤቱ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ውጤታማ ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም መደበኛ ውይይቶችን በማስቀጠል፣ ሰላማዊ እና የዘመነ የፖለቲካ ባህል እንዲኖር በመተባበር ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ዛሬ ጠዋት በሸገር ከተማ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም