በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል
ጂንካ፤ሰኔ 25/2018(ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጥ ዘር አቅርቦትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማረጋገጥ ትኩረት መስጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት በአሪ ዞን በደቡብ አሪ ወረዳ ጨለጎድ ቀበሌ ለምርጥ ዘር ብዜት የሚውል 1 ሺህ ሄክታር መሬት ተረክቧል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ግዳልቅ አልቅሚ በወቅቱ እንደገለፁት፤ በክልሉ ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ለምርጥ ዘር ብዜት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
የምርጥ ዘር ብዜቱን በማስፋት የክልሉን ፍላጎት ከመሸፈን ባለፈ ለሌሎች ክልሎች ለመትረፍ የተጨማሪ መሬት ርክክብ መከናወኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ያመለከቱት ደግሞ የክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ግዛው ናቸው።
ድርጅቱ በተለያዩ ማዕከላትና በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ምርጥ ዘር እያለማ መሆኑን አንስተው፤ ዛሬ ርክክብ የተደረገው መሬትም በቀጣይ የምርጥ ዘር አቅርቦት ሽፋኑን ለማሳደግ እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሪ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ አፌዶ ወርቁ በበኩላቸው፤ በክልሉ የተጀመረው የምርጥ ዘር ብዜት ንቅናቄ በዞኑ ያለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት እንደሚያሰፋው ጠቅሰዋል።
ዛሬ ርክክብ የተካሄደበት መሬትም የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትና የስራ ዕድል ፈጠራን የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመዋል።
በወረዳው በደጋማ አካባቢዎች የስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት በአርሶ አደር ማሳና በኮርፖሬት ኢንቨስትመንት በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የደቡብ አሪ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ደኢዶቆ ናቸው።
በዚህ የምርጥ ዘር ብዜት መሬት ርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።