ቀጥታ፡

ጥብቅ የተፈጥሮ ሀብት ቦታዎችን በማልማት ለሀገሪቱ የቱሪዝም እድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ)፦መንግስት ጥብቅ የተፈጥሮ ሀብት ቦታዎችን በማልማት ለሀገሪቱ የቱሪዝም እድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ ይበልጥ ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማስተዳደር የሚያስችሉ የጂኦስፓሻል ፕላት ፎርም እና የአትላስ የመረጃ ስርዓት ይፋ ተደርገዋል፡፡


 

ስርዓቱን የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያለሙት ሲሆን አሁን ላይ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና በሰንቀሌ ስዌይን ሀርትቢስት (የቆርኪዎች) ጥበቃ በስራ ላይ የሚውል ሲሆን በቀጣይም በኢትዮጵያ በሚገኙ ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎች ይተገበራል ተብሏል፡፡

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፣ ኢትዮጵያ ወደ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" በምታደርገው ጉዞ የቱሪዝም ዘርፉን ለማዘመን በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእነዚህም መካከል የሀገሪቱን የዱር እንስሳት ሀብት መረጃ በቴክኖሎጂ ማዘመንና ሌሎችም ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።


 

ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎችን በማልማት፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እና ፓርኮችን በአግባቡ በመጠበቅ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን ድርሻ ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው ቴክኖሎጂም ይህንን ጥረት በማገዝ ቱሪስቶች ስለ ብዝሃ ህይወት ስርጭት እና ስለ ቦታዎቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በቀላሉ መረጃ አግኝተው ጉብኝታቸውን እንዲያቅዱ ጉልህ ሚና ይጫወታል ሲሉ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎችን በዲጂታላይዜሽን መንገድ ለመጠበቅና መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል ድረ-ገጽን መሠረት ያደረገ የጂኦስፓሻል ፕላትፎርም እና አትላስ ወደ ስራ መግባቱ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አክለዋል።

ይህ አሰራር በተለይም ጎብኚዎች የተለያዩ የብዝሃ ህይወት ሀብቶች የሚገኙባቸውን ስፍራዎች በቀላሉ ለመለየት እንዲሁም ስለ ቦታዎቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በቂ መረጃ አግኝተው መሄድ ወደሚፈልጉት ጥብቅ ስፍራዎች እንዲጓዙ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።


 

የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለቱሪዝም እና ለኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሚሆኑ በርካታ የተፈጥሮ የብዝሃ ህይወት ጸጋዎች ባለቤት ናት ብለዋል፡፡

ሆኖም እነዚህን ሀብቶች ከዘመኑ ጋር በሚመጥን መልኩ በመረጃ የማስተዳደርና የመጠበቅ ሥራዎች ክፍተት እንደነበሩባቸው ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ይህንን ችግር ለመቅረፍም ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ፕላትፎርሙን ማበልጸጉን ገልጸዋል።

ይህ ጂኦስፓሻል ፕላትፎርም በመጀመሪያው ምዕራፍ የሁለት ጥብቅ ቦታዎችን ማለትም የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን እና የሰንቀሌ ስዌይን ሀርትቢስት (የቆርኪዎች) መጠለያን መረጃዎች ያካተተ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጂራ፥ ቴክኖሎጂው ተቋማቸው በሀገሪቱ ያሉ የዱር እንስሳት ሀብቶችን እና ጥብቅ ቦታዎችን በመረጃ ላይ በተደገፈ መንገድ ለመጠበቅ ያለውን አቅም እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።

በቀጣይ በሀገራችን የሚገኙትን ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎች በሙሉ በቴክኖሎጂ ለማዘመን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም