ቀጥታ፡

በክልሉ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ያለውን ዕምቅ አቅም ለመጠቀም የተደረጉ ጥረቶች ውጤት አስመዝገበዋል

ሆሳዕና፤ ሰኔ 25/2018 (ኢዜአ) ፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ያለውን ዕምቅ አቅም በመጠቀም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተደረጉ ጥረቶች ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ በእንስሳትና ዓሳ ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎችን የሚገመግም መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሄዷል።


 

በወቅቱም የቢሮው ምክትል ኃላፊና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ እያሱ ተረፈ እንዳሉት፤ በክልሉ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ያለውን ዕምቅ አቅም በመጠቀም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ 

ለአብነትም የወተት ሀብት ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት፣ ምርቱ ከቤት ፍጆታ አልፎ አሁን ላይ ስምንት የወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። 

ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት ረገድ እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በቢሮው የእንስሳትና ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በክልሉ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 


 

በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ በመኖ ልማት፣ በማሽነሪና በቴክኖሎጂ ሽግግር አርሶ አደሩን በህብረት ስራ ማህበራት በማደራጀት በተቀናጀ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም በክልሉ በዘርፉ የተሰማሩ 57 የህብረት ስራ ማህበራትን እና ከ219 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በቀጥታ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋልታ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ያሲን ሀሰን፤ ዩኒየኑ በተደረገለት ድጋፍ በዶሮ እርባታና በእንስሳት መኖ ማቀነባበር ዘርፍ ተሰማርቶ ተጨማሪ ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ዘርፉ ያለውን አቅም ለማጠናከር የተጀመረው ጥረት ገበያን ለማረጋጋት ያስቻለ ምርት እያስገኘ መሆኑን አንስተው፣ በዚህ ዓመት ብቻ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ እንቁላል ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸው እንዲጨምር መደረጉን ጠቁመዋል።

በተሰማሩበት የእንስሳት እርባታ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ በዝርያ ማሻሻል ረገድ በተደረገላቸው ድጋፍ ስኬታማ እየሆኑ ስለመምጣታቸው የተናገሩት ደግሞ በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዘነበች ጋርከቦ ናቸው። 


 

በቀን እስከ 50 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፣ በዚህም ልጆቻቸውን ከማስተማር ባለፈ ለነገ የሚሆናቸውን ተጨማሪ ሀብት እንዲያፈሩ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው አስረድተዋል።

በዚህ የምክክር መድረክ መርሐ ግብር ላይ የክልልና የዞኖች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም